የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎትን በ"ኦን ላይን" ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ነው

ባህር ዳር መጋቢት 21/2014(ኢዜአ) የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎትን በ"ኦን ላይን" በመስጠት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።

በተሻሻለው የንግድ ህግ እና ኦን ላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተዘጋጀ የምክክር መድረከ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሐመድ በመድረኩ መክፈቻ ላይ እንደገለጹት፣ ሚንስቴሩ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ከሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ በ"ኦን ላይን" ለመስጠት  ዝግጅት እያደረገ ነው።

አገልግሎቱ በኦን ላይን መሰጠቱ ቀደም ሲል የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ለማግኘት ይወስድ የነበረውን ጊዜ፣ ወጪና እንግልት እንደሚያስቀር ተናግረዋል።

"የደንበኞችን ምልልስ እና የሙስና ተጋላጭነትን ከማስቀረት ባለፈ ወደንግድ ስራ የሚገቡ አዳዲስ ነጋዴዎችን በመሳብ መደበኛና ዘመናዊ ንግድን ለማስፋፋት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል" ብለዋል።

በተጨማሪም እስካሁን የሚስተዋሉትን የመረጃ አያያዝና አደረጃጀት ክፍተቶች በማስተካከል ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለደንበኞች ለመስጠት እንደሚያስችል ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያስታወቁት።

በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያለውን የግብይት ስርዓት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ በማድረግ ኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት ተመራጭ እንድትሆን ለማድረግ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።

በ1952 ዓመት የወጣውና እስካሁን ሲሰራበት የቆየው የንግድ ህግ ባለፈው ዓመት እንዲሻሻል መደረጉንም አሰታውሰዋል።

"ይህም ለውጭ ገበያ የሚላኩ ምርቶችን በመጠንና በዓይነት በማሳደግ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በማስፋት በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች የተያዙ ግቦችን ለማሳካት ያግዛል" ብለዋል።

ዛሬ የተጀመረው  መድረክ በአዲሱ የኦን ላይን ምዝገባ እና በተሻሻለው ህግ ላይ በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ግንዛቤ ይዘው ፈጥነው ወደ ሥራ እንዲገቡ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

"የተሻሻለውን ህግ በተሟላ መንገድ ለማስፈፀምና አዳዲስ አሰራሮችን ለመተግበር የባለሙያዎችን አቅም ማሳደግ አስፈላጊ ነው" ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቀለመወርቅ ምህረቴ ናቸው።

የንግድ ስርዓቱን በአግባቡ መምራት የሚቻለው የተሻለ ግንዛቤ ሲኖር በመሆኑ ሚኒስቴሩ የጀመረውን የአቅም ግንባታ ስራ  አጠናክሮ እንዲቀጥልም  ጠይቀዋል።

 ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨባጫ መድረኩ ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ የንግድ ዘርፍ  አመራሮችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ኢዜአ ከባህር ዳር ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም