አካዳሚው የበጀት ጉድለቱን በፍጥነት ማስተካከል እንደሚገባው ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
አካዳሚው የበጀት ጉድለቱን በፍጥነት ማስተካከል እንደሚገባው ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ
መጋቢት 21/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የበጀት ጉድለቱን በፍጥነት ማስተካከል እንደሚገባው የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የስፖርት አካዳሚ የ2012 በጀት ዓመት የሂሳብ ኦዲት ሪፖርት ላይ ውይይት አድርጓል።
ቋሚ ኮሚቴው የአካዳሚውን የወጪ ሂሳብ፣ የተከፋይ ሂሳብ፣ የሂሳብ መደቡን ያልጠበቀ የወጪ ሂሳብ እንዲሁም በጀትና ንብረት አስተዳደርን በተመለከተ ያገኘው የበጀት ጉድለት መስተካከል እንደሚገባው አንስቷል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ክርስትያን ታደለ እንደተናገሩት፤ አካዳሚው የተገኘበትን የበጀት ጉድለት በፍጥነት ማሰተካከል ይገባዋል ።
አካዳሚው የተመደበለትን በጀት ጭምር በአግባቡ ጥቅም ላይ አለማዋሉን የተናገሩት ሰብሳቢው፤ ከተመደበለት በጀት በላይ ተጠቅሞ መገኘቱንም አንስተዋል።
በዚህም አካዳሚው ከተፈቀደለት በጀት ተጨማሪ 208ሺ ብር ተጠቅሞ መገኘቱን የኦዲት ሪፖርቱ እንደሚያሳይ ገልፀዋል።
አካዳሚው በ2012 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ባዘጋጀው ውይይት ላይም ለ19 ሠራተኞች 39 ሺ 128 ብር ያለ አግባብ የውሎ አበል መከፈሉንም ተናግረዋል።
የሂሳብ መደቡን ያልጠበቀ በወጪ ሂሳብ ረገድም 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር የበጀት አርዕስቱን ያልጠበቀ የወጪ ምዝገባ መከናወኑም ለአብነት አንስተዋል።
የበጀት ጉድለቱን ያስከተሉ አካላት በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ተገቢው አስተዳደራዊ እርምጃ እስከ ሚያዚያ 7 ቀን 2014 ዓ.ም እንዲወሰድ አሳስበዋል።
ሂደቱ ምን ላይ እንደደረሰም ለቋሚ ኮሚቴው ዝርዝር ሪፖርት እንዲያቀርብ መወሰኑንም ገልፀዋል።
በአጠቃላይ የስፖርት አካዳሚ የተገኘበትን የበጀት ጉድለት ፈጥኖ እንዲያስተካከል ቋሚ ኮሚቴው እንደሚያሳስብ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የኦዲት ግኝት ማስተካከያዎችን ደግሞ በ100 ቀናት ዕቅድ ውስጥ እንዲካተቱ መደረግ እንዳለበትም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አቶ አንበሳው እንየው በበኩላቸው በኦዲት ሪፖርቱ የታዩ ችግሮችን ለማረምና በአሰራር ላይ የታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል ይሰራል ብለዋል።
የመንግስት በጀት ተመድቦ ጥቅም ላይ ያልዋለበትን ምክንያት በኮቪድ 19ን ጨምሮ በአገሪቷ የተለያዩ ችግሮች በመከሰታቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ከተፈቀደ ዓመታዊ በጀት በላይ ወጪ ለመደረጉም ልዩ ልዩ ምክንያቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ አካዳሚው 208ሺ ብር ከበጀት በላይ አለመጠቀሙንና ችግሩ የተከሰተው በበጀት ምዝገባ ስህተት መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን ላይ ግን ችግሩ መስተካከሉንም አክለዋል።