ቀጥታ፡

ሙስናን ለመከላከል በዜጎች ሰብዕናና ስነ ምግባር ግንባታ ላይ በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል -ዶክተር ሳሙኤል ዑርቃቶ

አዳማ ፤ መጋቢት 21/2014(ኢዜአ) ሙስናንና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል በዜጎች ስብዕናና ስነ ምግባር ግንባታ ላይ በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ የፌዴራል ሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽነር ዶክተር ሳሙኤል ዑርቃቶ ተናገሩ።

"ሙስናን በመከላከል የመገናኛ ብዙሃንና የምርመራ ጋዜጠኞች  ሚና "  በሚል ርዕስ  ከክልሎችና ፌዴራል የመገናኛ ብዙሃን ለተውጣጡ አመራሮችና ባለሙያዎች ኮሚሽኑ ያዘጋጀው የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።

ኮሚሽነሩ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር  "ሙስና ከብልሹ አሰራርና ከስነ ምግባር ጉድለት የሚመነጭ የሌብነት ተግባር ነው" ብለዋል።

ከብልሹ አሰራር የፀዳ የመገናኛ ብዙሃን  ተቋማት በመገንባት ሀገርና ህዝብን ከሌብነትና ብዝበዛ የማዳን አቅም  መፍጠር እንደሚቻል ገልጸዋል።

በተለይም የዜጎችን ሰብዕናና ስነ ምግባር በመገንባት ረገድ የመገናኛ ብዙሃን  ተቋማት ሚና የላቀ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ሳሙኤል፤ ሙስናን ለመታገልም መጀመሪያ ራሳቸው ከብልሹ አሰራርና ሌብነት የፀዱ መሆን አለባቸው ነው ያሉት።

የመድረኩ ዓላማም ከሙስና የፀዳና ሌብነትን የሚፀየፍ ትውልድ ለመፍጠር ማስተማር ቅድሚያ የሚሰጠው በመሆኑ ከመገናኛ ብዙሃን  ተቋማት አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር አጀንዳውን የጋራ ለማድረግ መሆኑን አስረድተዋል።

በኮሚሽኑ የማቴሪያል ዝግጅትና የስነ ምግባር ግንባታ መምሪያ ሃላፊ አቶ አክሊሉ ሙሉጌታ፤ የመገናኛ ብዙሃን  ተቋማት ስለ ሙስና ከማውራታቸው ባለፈ ራሳቸው ከሙስናና ብልሹ አሰራር የፀዱ መሆናቸውን ማጥናት ያስፈልጋል ብለዋል።

ማህበረሰቡን ከሙስናና ብልሹ አሰራሮች ለመጠበቅ  መገናኛ ብዙሃን ያላቸውን ሚና መወጣት የሚችሉት ራሳቸውን ከመሰል ድርጊት ጠብቀው የሞራል ልዕልና ሲኖራቸው ብቻ መሆኑን የሚያነሱት ደግሞ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ኢድሪስ ናቸው።

''ከሚዲያው የህዝብን ፍላጎቶች መሰረት ያደረጉ ፕሮግራሞችና የምርመራ ስራ መስራት ይጠበቃል'' ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለዚህም ትክክለኛ አሰራርና ስርዓት መከተል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም