ቀጥታ፡

የኢጋድ አባል አገራት የ'ብሉ ኢኮኖሚ' ዘርፍ የጋራ ተጠቃሚነት እንዲያድግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

መጋቢት 21/2014/ኢዜአ/  የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ቀጣናዊ ትብብርን በማጠናከር የአባል አገራቱ የ'ብሉ ኢኮኖሚ' ዘርፍ የጋራ ተጠቃሚነት እንዲያድግ እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

'ብሉ ኢኮኖሚ' የውቅያኖስ፣ የሀይቅና የባህር ሀብቶችን እንዲሁም ወደቦችን ዘላቂነት ባለው መልኩ ጥቅም ላይ ማዋልን ማዕከል ያደረገ ነው።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ባዘጋጀው የ'ብሉ ኢኮኖሚ' ስትራቴጂ ዙሪያ በአዲስ አበባ መክሯል።

ስትራቴጂው በትራንስፖርት፣ በቱሪዝም፣ በአሳ ሀብት ልማትና በሌሎች አካታችና ዘላቂ የውቅያኖስ፣ የሀይቅና የባህር ሀብቶች አጠቃቀም ለመዘርጋት ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።

የባለስልጣኑ የአካባቢ ጥበቃና የ'ብሉ ኢኮኖሚ' ፕሮግራም ኃላፊ ዶክተር እሸቴ ደጀኔ፤ ዘርፉን በዘላቂነትና በትብብር መጠቀም የሚያስችል መዋቅር ለመዘርጋት እስትራቴጂ ተቀርጾ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በዚህም አባል አገራቱ በቱሪዝም፣ በአሳ ሀብት ልማት፣ በማሪታይም ትራንስፖርት፣ በወደብ አጠቃቀምና ሌሎች የ'ብሉ ኢኮኖሚ' ሀብቶች የጋራ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሰራ እንደሆነም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን የዓለም አቀፍ ህግ ባለሙያ ወይዘሪት አነኔ ቀጀላ፤ ኢትዮጵያ 'ብሉ ኢኮኖሚ' የሚያተኩርባቸው ዘርፎች ላይ ስትራቴጂ እየቀረጸች መሆኑን ገልጸዋል።

ወደብ አልባ የሆነችው ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የውኃ ክልሎችን ጨምሮ የጎረቤት አገሮችን የውቅያኖስ ሀብት የመጠቀም ሙሉ መብት በዓለም አቀፍ ስምምነት መሰጠቱን አውስተዋል።

በተለይም በወደብ ጉዳይ ከኢጋድ አባል አገራት ጋር በትብብር ለመጠቀም እየሰራች መሆኑን አስረድተዋል።

የሶማሊያ ብሔራዊ ማሪታይም አስተባባሪና የብሉ ኢኮኖሚ ዳይሬክተር ሙንታዚያህ ጀማሌ በበኩላቸው፤ አገራቸው የዘርፉን ኃብት በጋራ ለመጠቀም ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።

ሶማሊያ በዘርፉ ያላትን ኃብት ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአባል አገራት ጋር በትብብር ለመጠቀም ዝግጁ እንደሆነች አረጋግጠዋል።

የኢጋድ ዋና ጸሀፊ ተወካይ ዳሃር ኢልሚ በበኩላቸው ስትራቴጂው ቀጣናዊ ትብብርን በማጠናከር ኢኮኖሚያዊ ውህደትን ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ያፋጥናል ብለዋል።

ስትራቴጂው እንደ አውሮፖውያን አቆጣጠር ከ2021 እስከ 2025 ዓ.ም ተግባራዊ እንደሚሆንም ታውቋል።

የኢጋድ አባል ሀገራት ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት የሚበጃቸውን ስትራቴጂ እንደሚቀርጹም ተመልክቷል።

በኢጋድ የተዘጋጀው 'ብሉ ኢኮኖሚ' ስትራቴጂ የፊታችን አርብ ጉዳዩ በሚመለከታቸው የአባል አገራት ሚኒስትሮች እንደሚጸድቅ ይጠበቃል።

የአፍሪካ ሕብረት በአጀንዳ 2063 ውስጥ ቅድሚያ ከሰጣቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ 'ብሉ ኢኮኖሚ' ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም