ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ኤርትራ ገቡ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ኤርትራ ገቡ
አሰብ ኤርትራ ነሀሴ 30/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የቻይና አፍሪካ ጉባዔን አጠናቀው ዛሬ ማለዳ ኤርትራ ገብተዋል። የኤርትራው ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ በአሰብ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት አቀባበል አድርገውላቸዋል። ዶክተር አብይ አህመድ በሚኖራቸው ቆይታ አሰብና ምጽዋን እየጎበኙ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በስፍራው ለተገኙ ጋዜጠኞች እንደገለጹት፤ የአሰብና ምጽዋ መንገዶችና ወደቦች ስራ ለመጀመር ዝግጁ ናቸው። ከቻይና የአፍሪካ ጉባዔ በቀጥታ ወደ ኤርትራ ያመሩት ከአፍሪካውያን መሪዎች ጋር ቀጣናዊ ውህደት ለመፍጠር የተጀመረውን ውይይት በማስቀጠል ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር ለመወያየት መሆኑን ነው የገለጹት። በቀጣናው ሰላም ማስፈን ብቻ በቂ ያለመሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአካባቢው ያለውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለማፋጠን የሚያስችሉ ስራዎች መከናወን እንዳለባቸው ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ለሃያ ዓመታት የነበራትን "ሞት አልባ ጦርነት" ወደ ሰላም ለመቀየር እንቅስቃሴ መጀመራቸው ይታወሳል። ሐምሌ መጀመሪያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ወደ ኤርትራ በማቅናት ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጋር ተወያይተዋል፤ በውይይቱም በሁለቱ አገሮች መካከል ላለፉት 20 ዓመታት ተቋርጦ የቆየውን ግንኙነት ለማስቀጠል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወቃል። በምክክራቸው ወደብ መጠቀምን ጨምሮ የዲፕሎማሲ ግንኙነት መጀመር፣ ዜጎች በነፃነት መንቀሳቀስ እንዲችሉና የሁለቱ አገሮች አየር መንገዶች መደበኛ በረራ እንዲያደርጉ ስምምነት ላይም ደርሰዋል።