ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን የሚመስል መዋቅራዊ አደረጃጀትና ስያሜ ተዘጋጅቷል- የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ

መጋቢት 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) የፌደራል ፖሊስ ኢትዮጵያን የሚመስል መዋቅራዊ አደረጃጀትና ስያሜ አዘጋጅቶ በመካከለኛ ደረጃ ለተመደቡ አመራሮች የመሪነት ስልጠና መስጠቱን አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በዋና ክፍል የተመደቡት መካከለኛ አመራሮች በተመደቡበት የሥራ መስክ የአደረጃጀትና የትራንስፎርሜሽን መሪ ሚናን በሚገባ ተረድተው የተቋሙን የ10 ዓመት ዕቅድ ለማስፈፀም የሚያስችል አቅም እንዲፈጥሩ በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ወስደዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በስልጠናው መክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ ተገኝተው ለሰልጣኞች መልዕክት በማስተላለፍ የተቋሙን የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድና የፀጥታ ዘርፍ የለውጥ ፅንሰ ሃሳብ ላይ ግንዛቤ አስጨብጠዋል።

በተጨማሪም በፖሊስ አሰራር ጥሩ ልምድ ያላቸው ሀገሮች ተሞክሮን እንዴት መጠቀም እንደሚገባ አብራርተዋል።

የወንጀል መከላከል ስራችን በዓለም ላይ ተግባራዊ ሆኖ ውጤት ካስገኙ ስትራቴጂክ ፖሊሲንግ ሞዴሎች ውስጥ የማህበረሰብ አቀፍና መረጃ መር የፖሊስ ወንጀል መከላከል ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልፀዋል፡፡

ሰልጣኝ መኮንኖቹም በስልጠና ቆይታቸው በሪፎርም ምንነት፣የተቋሙን የ10 ዓመት ዕቅድ፣ ተቋማዊ አደረጃጀት፣ በንብረት አያያዝ፣ በበጀት አጠቃቀም፣ በተሻሻለው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ፣ በፖሊስ ዶክትሪንና በአመራርነት ክህሎት ማሳደግ፣ እንዲሁም የቴክኖሎጂ አጠቃቀም አቅምን በማሳደግ የወንጀል መከላከልና የምርመራ ሥራዎች ማከናወን እንደሚገባ፣ የፖሊስ ስነ-ምግባር ምን መምሰል እንዳለበትና ሰፊ ማብራሪያና ትምህርት መውሰዳቸውን ገልፀዋል።

በፖሊስ የአመራሩና አባላቱ የነበሩ መሰረታዊ ችግሮች በየደረጃው እንደሚፈቱና የተሻለ ቁመና ያለው ተቋም እንዲገነባ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ገልጸዋል።

የመሪነት አቅም ማጎልበቻ ስልጠናው በቀጣይም እስከ ታችኛው የአመራር እርከንና አባላት ድረስ እንደሚሰጥ ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም