አካል ጉዳተኝነት የትኛውንም ዓላማ ከማሳካት አያግድም፤ የሚገጥሙንን ችግሮች ተቋቁመን ለስኬት መብቃት እንችላለን - ኢዜአ አማርኛ
አካል ጉዳተኝነት የትኛውንም ዓላማ ከማሳካት አያግድም፤ የሚገጥሙንን ችግሮች ተቋቁመን ለስኬት መብቃት እንችላለን
መጋቢት 20/2014 /ኢዜአ / ''አካል ጉዳተኝነት የትኛውንም ዓላማ ከማሳካት አያግድም፤ የሚገጥሙንን ችግሮች ተቋቁመን ለስኬት መብቃት እንችላለን'' ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው አካል ጉዳተኞች ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ህጻናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሴት አካል ጉዳተኞች የእርስ በእርስ ልምድ ልውውጥ መድረክ አካሂዷል፡፡
የመድረኩ ዋነኛ ዓላማ አካል ጉዳተኞች የሚገጥሟቸውን ችግሮች ተቋቁመው ለስኬት የሚበቁበትን ልምድ ማካፈል ሲሆን፤ የገጠሟቸውን ችግሮች ተቋቁመው ለስኬት የበቁ አካል ጉዳተኞች ልምዶቻቸውን አጋርተዋል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎች አካል ጉዳተኝነት ያሰቡትን ህልም ከማሳካት እንደማያግድ ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮ ሃና ሞገስ አካል ጉዳተኝነት በማንኛውም ሰው ላይ ሊከሰት የሚችል መሆኑን ጠቁመው፤ አካል ጉዳተኞች የትኛውንም አይነት ችግር ተቋቁመው ስኬት ማስመዝገብ እንደሚችሉ ነው የገለጹት፡፡
እርሳቸው አካል ጉዳተኝነት ሳያግዳቸው ተምረው ከፈለጉበት ደረጃ መድረሳቸውንም ነው ያነሱት፡፡
አካል ጉዳተኞች ስኬታማ እንዲሆኑ አሳታፊና አካታች ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በመድረኩ ልምዱን ያካፈለው የህግ ባለሙያው ወጣት ዳግማዊ አሰፋ በበኩሉ በመኪና አደጋ ለአካል ጉዳት መዳረጉን ገልጾ፤ ይህም ያሰበውን ከማሳካት እንዳላገደውና በአሁኑ ወቅት አገሩን በህግ ሙያ እያገለገለ እንደሚገኝ ነው የተናገረው፡፡
"ሰውን ለስኬት የሚያበቃው አስተሳሰቡ ነው" የሚለው ወጣት ዳግማዊ፤ ማንኛውም ሰው ዓላማውን ለማሳካት በርትቶ ከሰራ ለስኬት እንደሚበቃ ተናግሯል፡፡
በመሆኑም አልችልም የሚል አስተሳሰብ ሊወገድ ይገባል ነው ያለው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ህጻናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሃና የሽንጉስ፤ ቢሮው ሴት አካል ጉዳተኞችን በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማህበራዊ ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ቢሮው አካል ጉዳተኞችን የሚመለከቱ አዋጆችና ድንጋጌዎች በአግባቡ ተፈጻሚ እንዲሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
መድረኩ አካል ጉዳተኞች ሰርተው ለስኬት መብቃት እንደሚችሉ የሞራል መነሳሳትን የሚፈጥር መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡