ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና አዳዲስ ክብረ ወሰኖች ተመዘገቡ

መጋቢት 20/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በመጀመሪያው ቀን በተደረጉ ሦስት የፍፃሜ ውድድሮች አዲስ ክብረ ወሰን ተመዝግቧል።

51ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታዲየም እየተካሄደ ይገኛል።

ትናንት በተካሄደው የመጀመሪያ ቀን ውድድሮች የ10 ሺህ ሜትር የወንዶች ሩጫ፣ የወንዶች ሱሉስ ዝላይና የሴቶች አሎሎ ውርወራ ፍፃሜ ተካሂዷል።

በሶስቱም የፍፃሜ ውድድሮች አዲስ ክብረወሰን ተመዝግቧል።

በ10 ሺህ ሜትር የወንዶች በ1996 ዓ.ም በአትሌት ስለሺ ስህን ተይዞ የነበረው 28  ደቂቃ 16 ሴኮንደ ከ 23 ማይክሮ ሰከንድ ክበር ወሰን፤ ከ18 ዓመት በኋላ አትሌት ታደሰ ወርቁ  28 ደቂቃ 11 ሰከንድ 92 ማይክሮ ሰከንድ አሻሽሎታል።

በወንዶች ሱሉስ ዝላይ በ2011 ዓ.ም በአትሌት ዐዲር ጉር 15 ነጥብ 88  ሜትር ተይዞ የነበረው ክብረ ወሰን 'ኢትዮጵያ ኤሌክት አትሌት' የሆነው ክችማን ኦጅሉ 16 ነጥብ 03 በመዝለል አዲስ ክብረ ወሰነ አስመዝግቧል።

በሴቶች አሎሎ ውርወራ አትሌት ዙርጋ ኡስማን በ2011 ዓ.ም በራሷ ተመዝግቦ የነበረውን ክብረ ወሰን አሻሽላዋለች።

አትሌት ዙርጋ ከዚህ በፊት 13 ነጥብ 55 በመወርወር የነበረው ክብረ ወሰን 13 ነጥብ 56 በመወርወር የራሷን ክብረ ወሰን እንዳሻሻለችው ታውቋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከአንድ እስከ ሦስተኛ ሆነው ለሚያጠናቅቁ አትሌቶች 3 ሺህ 500 ብር፣ 2 ሺህ 500  ብር እና 2 ሺህ ብር እንደየቅደም ተከተላቸው የገንዘብ ሽልማት ተሰጥቷል።

ከዚህ  በተጨማሪ አዲስ  ክብረወሰን ላሻሻሉ አትሌቶች 7 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት ይሰጣል።

አትሌት ክችማን ኦጅሉ እና አትሌት ዙርጋ ኡስማን የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ በመሆናቸውና ክብረወሰን በመስበራቸዉ እያንዳንዳቸው 10 ሺህ 500  ብር ተሸላሚ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም