ቀጥታ፡

የእውቁ የምጣኔ ሃብት ምሁር ፕሮፌሰር ተሾመ ሙላት መገልገያ የነበሩ ከ1 ሺህ 800 በላይ መጻሐፍት ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተበረከቱ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት እውቁ የምጣኔ ሃብት ምሁር ፕሮፌሰር ተሾመ ሙላት መገልገያ የነበሩ ከ1 ሺህ 800 በላይ መጻሐፍት ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተበረከቱ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለግማሽ ምዕተ ዓመት በአስተማሪነትና ተመራማሪነት ያገለገሉት ጎምቱው የምጣኔ ሃብት ምሁር ፕሮፌሰር ተሾመ ሙላት ባጋጠማቸው የጤና እክል በቅርቡ በ80 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

የፕሮፌሰሩ ቤተሰቦችም ምሁሩ በህይወት ዘመናቸው ለምርምርና ለማስተማሪያ ማጣቀሻነት ሲገለገሉባቸው የነበሩ 1 ሺህ 838 ልዩ ልዩ መጻህፍትን ባላገለገሉት የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል አስረክበዋል።

መጻህፍቱ ፕሮፌሰሩ ወደ ትምህርት ዓለም ከገቡበት ጀምሮ የተሰበሰቡ ሲሆን በተለይም የተማሪዎችን የምርምር ችሎታ በማሳደግ በኩል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ ተገልጿል።

የመጻሃፍት ስጦታውን የተረከቡት በዩኒቨርሲቲው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶክተር አጥናፉ ገብረመስቀል መጻህፍቱ የኢኮኖሚክስ፣ የታሪክ እና ተያያዥነት ያላቸው እንደሆኑ ገልጸዋል።

ፕሮፌሰር ተሾመ ሙላት የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል አሁን ላይ የደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ ሙሉ ጊዜያቸውና ጉልበታቸውን በመስጠት  ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ምሁር እንደነበሩም መስክረዋል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚስቶች ማህበርን ካቋቋሙ ምሁራን አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ተሾመ ኢትዮጵያን ወክለው በዓለም አቀፉ ሰራተኞች ድርጅት፣ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና መሰል ዓለም አቀፍ መድረኮች ማገልገላቸውን ጠቁመዋል፡፡

የፕሮፌሰሩ ቤተሰቦች መጻህፍቱን ለመጪው ትውልድ ይጠቅማሉ ብለው በማሰብ በራሳቸው ተነሳሽነት መጥተው በማስረከባቸውም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የፕሮፌሰር ተሾመ ሙላት ወንድም አስራት ሙላት ለዩኒቨርሲቲው የተሰጡት መጻሃፍት በወንድማቸው መኖሪያ ቤት ተከማችተው የነበሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ በሌሎች ቦታዎች የሚገኙ መጻህፍትንም በቀጣይ እንደሚያስረክቡ ገልጸዋል።

ወንድማቸው ሙሉ ጊዜያቸው ለትምህርት የሰጡ አገር ወዳድ አንባቢ፣ እጅግ ሲበዛ ጠንቃቃና ትክክለኛ የሆነ ነገር ፈላጊ ሰው እንደነበሩም ጠቅሰዋል፡፡

በስጦታ የተበረከቱት መጻሃፍት የኢኮኖሚክስ ትምህርት ፍልስፍና ከተጀመረበት ጊዜ እስከ አሁን ያለውን ደረጃ የሚዳስሱ በመሆናቸው የተማሪዎችን የምርምር ችሎታ በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖራቸውም ዶክተር አጥናፉ ተናግረዋል፡፡

ፕሮፌሰር ተሾመ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በ1964፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከአሜሪካው ሰሜን ምዕራብ ዩኒቨርሲቲ በ1966 ተቀብለዋል።

የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከእንግሊዙ ማንቸስተር ዩኒቨርሲቲ በ1971 የተቀበሉ ሲሆን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ጆርናል የአማካሪ ምክር ቤት አባል በመሆን አገለግለዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍልን በኃላፊነት፣ በተመራማሪነትና በአማካሪነት እንዲሁም በኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስቴር እንዲሁ በአማካሪነት ሰርተዋል፡፡

ፕሮፌሰር ተሾመ ሙላቱ በዘርፉ ላይ ባደረጉት የጥናት እና ምርምር ስራም 3 መጻህፍትን እና ከ50 በላይ የጥናት እና ምርምር ስራዎችን ለህትመት አብቅተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም