ቀጥታ፡

የወደሙ ጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም የሆስፒታሎች ጥምረት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል- የጤና ሚኒስቴር

ደሴ ፤ መጋቢት 20/2014 (ኢዜአ) መንግስት በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ ጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም በሚያርገው ጥረት የሆስፒታሎች ጥምረት ከፍተኛ ሚና መጫወቱን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

 "የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት" በሚል መሪ ሀሳብ የሆስፒታሎችን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የሚያግዝ  አራተኛው ዙር የምክክር መድረክ በደቡብ ወሎ ኮምቦልቻ ከተማ ተካሂዷል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ፤ሆስፒታሎች ጥምረት እንዲፈጥሩ የተደረገው በቴክኖሎጂ በመታገዝ ተደጋግፈውና ልምድ በመለዋወጥ ፈጣን አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል ነው።

"የተሻለ አቅም፣ ልምድ፣ ቴክኖሎጂ፣ ግብዓትና አፈጻጸም ያላቸው ሆስፒታሎች ሌሎችን እንዲያግዙ መደረጉ የሆስፒታሎችን አቅም ከማሳደግ ባለፈ አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን አግዟል" ብለዋል።

በተለይ በአማራ እና አፋር ክልሎች በአሸባሪው ህወሓት የተዘረፉና የወደሙ ጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት መንግስትን በማገዝ  ከፍተኛ  ሚና መጫወቱን  ነው ያመለከቱት።

ዶክተር አየለ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች የሚገኙ  ሆስፒታሎች በአሸባሪው የወደሙትን መልሰው እንዲያቋቁሙ ትስስር መፈጠሩ የተጎዱ ጤና ተቋማት በከፊልም ቢሆን ሥራ እንዲጀምሩ አስችሏል።

በከፊል ሥራ የጀመሩት በአማራና አፋር  ክልሎች በየደረጃው የሚገኙ ከ2 ሺህ 900 በላይ  የጤና ተቋማት መሆናቸውን አመልክተዋል።

በዚህም የህብረተሰቡን እንግልት መቀነሰ እንደተቻለ ዶክተር አየለ አስረድተዋል።

እንደ አሳቸው ገለጻ፣ የጤና ተቋማትን ትስስር በማጠናከር የወደሙ ተቋማትን እስከ ቀጣይ ስድስት ወራት  ድረስ ሙሉ በሙሉ ወደ ነበሩበት አቅም እንዲመለሱ መንግስት በልዩ ትኩረት እየሰራ ነው።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ህይወት ደበበ  በበኩላቸው፤ በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ ጤና ተቋማት በሙሉ አቅማቸው ስራ እንዲጀምሩ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ዳያስፖራው፣ ባለሃብቱና ሌላው የህብረተሰብ ክፍል በተለያየ ቁሳቁስና ገንዘብ እየደገፈ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

"የሆስፒታሎች ጥምረት ፈጥረው በመንቀሳቀስ የወደሙትን መልሰው ከማቋቋም ባለፈ የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን እያጎለበቱ" ይገኛሉ ብለዋል።

"ወልድያ አጠቃላይ ሆስፒታል ሙሉ በሙሉ በአሸባሪው ህወሓት ቢወድምም መንግስት ሆስፒታሎችንና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር መልሶ እያቋቋመው ነው" ያሉት ደግሞ የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍስሃ የኋላ ናቸው።

ሆስፒታሉ በአሁኑ ወቅት ሁሉንም አገልግሎቶች መጀመሩን ጠቁመው፤ በቅርቡ ወደ ነበረበት ደረጃ ለመመለስ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ሆስፒታሉ ከጉዳቱ ተቋቋሞ  ለዚህ እንዲበቃ የሆስፒታሎች ጥምረት ከፍተኛ እገዛ ማድረጉን ጠቅሰው፣ "ቴክኖሎጂ እና ልምድ በመለዋወጥ አገልግሎት አሰጣጡን እያሻሻልን ነው" ብለዋል።

በመድረኩ የፌደራል፣ የክልልና የዞን አመራሮች፣ የተለያዩ ሆስፒታሎች ሥራ አስኪያጆችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም