ቤተ-ክርስቲያኗ በዳሰነች ወረዳ ተፈናቃይ ወገኖች ከ600 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገች - ኢዜአ አማርኛ
ቤተ-ክርስቲያኗ በዳሰነች ወረዳ ተፈናቃይ ወገኖች ከ600 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገች
ጂንካ፤መጋቢት 20/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ በተፈጥሮ ችግር ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ600 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ምግብ ነክ ድጋፍ አደረገች።
ድጋፉ ዘንድሮ በወረዳው በኦሞ ወንዝ ሙላትና ከዚያ በኋላ በተከሰተው ድርቅ ለተጎዱ ወገኖች እንደሚውል ዛሬ በተከናወነው የርክክብ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገልጿል።
የሀገረ ስብከቱ ዋና ስራ አስኪያጅ መላከ መንክራት ቆሞስ አባ ስምረተዓብ እሸቱ እንዳሉት፤ ድጋፉ የተሰባሰበው በአዲስ አበባና ሌሎች አካባቢዎች ከሚኖሩ ምዕመናን ነው።
በዚህም ከ600 ሺህ ብር በላይ የሚገመት 200 ኩንታል የበቆሎ ዱቄት በነብረሙስና በቡቡዋ ቀበሌዎች በጊዜያዊ መጠለያዎች ለሚገኙ 400 አርብቶ አደሮች ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ሀገረ ስብከቱ በወረዳው በድርቅና በጎርፍ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ ሲያደርግ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑንም አስታውሰዋል።
ቤተክርስቲያኗ በቀጣይም ምዕመናን በማስተባበር ማህበራዊ ሃላፊነቷን እንደምትወጣ አስታውቀዋል።
''ችግር የደረሰባቸውን ወገኖች መጠየቅ መንፈሳዊነትም ሰብአዊነትም ነው'' ያሉት ስራ አስኬያጁ፤ በሀገሪቱ በተከሰቱ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች መደገፍ ይገባል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የዳሰነች ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሞሪቴ ቶቦስ ፤ ለተደረገው ድጋፍ በተጎጂ ወገኖችና አስተዳደሩ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
ለወረዳው እየተደረገ ያለው ድጋፍ ከጉዳቱ መጠንና ስፋት አንፃር በቂ ባለመሆኑን ለተጎጂዎቹ የየዕለት ደራሽ ድጋፍ በማድረግና በዘላቂነት ለማቋቋም የፌዴራል መንግስትና ሌሎች አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በዳሰነች ወረዳ በዓመቱ መግቢያ ላይ በደረሰው ጎርፍና ከዚያም ተከትሎ በገባው ድርቅ ከመኖሪያ ቀዬያቸው ከተፈናቀሉት ወገኖች በተጨማሪ ለእንስሳትም የመኖ እጥረት ማጋጠሙ ተመልክቷል።