የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሥራ ማስኬጃ የሚውል 50 ሚሊዮን ብር ለፖለቲካ ፓርቲዎች ሊያከፋፍል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሥራ ማስኬጃ የሚውል 50 ሚሊዮን ብር ለፖለቲካ ፓርቲዎች ሊያከፋፍል ነው
አዲስ አበባ መጋቢት 20/2014 /ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሥራ ማስኬጃ የሚውል 50 ሚሊዮን ብር ለፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚያከፋፍል ገለጸ፡፡
ቦርዱ ይህን የገለጸው ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ባደረገው ውይይት ነው፡፡
በውይይቱም የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ ጊዜያት የሚያቀርቧቸውን አቤቱታዎች ምርምሮ እልባት ለመስጠት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ከፖለቲካ ፓርቲዎች የቀረቡለትን አቤቱታዎች በመንተራስ በርካታ ጥያቄዎች እልባት እንዲያገኙ ማድረጉን ገልጾ፣ ይህ ተግባር ቀጣይነት እንደሚኖረው ጠቁሟል፡፡
ጠቅላላ ጉባዔ ያደረጉ ፓርቲዎች ተሞክሮና ቀጣይ የሚያደርጉ ፓርቲዎች አካሄድ በሚሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚካሄድም ነው የተገለጸው፡፡
በተጨማሪም በመድረኩ መንግሥት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርገውን የገንዘብ ድጋፍ በሚመለከት ውይይት ተካሂዷል፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት አዲሱ የምርጫና የፖለቲካ ፖርቲዎች አዋጅ 1162/2011 መንግሥት ለፖለቲካ ፓርቲዎች በቋሚነት የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግ ይደነግጋል ብለዋል፡፡
በዚህ መሠረት ምርጫ ቦርዱ ለዚህ ዓመት ከመንግሥት 230 ሚሊዮን ብር ለማግኘት ጠይቆ አገሪቷ ካለችበት ወቅታዊ ችግር አንጻር ገንዘቡ እንደማይሰጥ እንደተገለጸላቸው ተናግረዋል።
ሆኖም ምርጫ ቦርዱ ባለፈው የምርጫ ወቅት ከወረቀት ህትመት የተረፈውን 50 ሚሊዮን ብር ለፓርቲዎች ለማከፋፈል ከመንግሥት ፈቃድ ማግኘቱን ገልጸዋል።
ገንዘቡ 30 በመቶ ለአገራዊ ፖርቲዎች፣ 20 በመቶው ለክልላዊ ፓርቲዎች እንዲሁም በፓርቲዎች የሴትና የአካል ጉዳተኞች አመራሮች ብዛት ታይቶ እንደሚከፋፈልም ገልጸዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ወቅት ያገኙት ውጤትና አሁን ላይ ያላቸው የስራ እንቅስቃሴም ከግምት ውስጥ እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም የፓርቲዎች ከዚህ ቀደም የነበራቸው የገንዘብ አጠቃቀምና የኦዲት ሪፖርትም እንዲሁ፡፡
በቀጣይም ለፖለቲካ ፓርቲዎች የቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚደረግም በውይይቱ ወቅት ተጠቁሟል፡፡