ቀጥታ፡

የምርምር ተቋማት የሚሰሯቸው የጥናትና ምርምር ሥራዎች የአሰራር ሥነ-ምግባርን የተከተሉ ሊሆኑ ይገባል

 አዲስ አበባ መጋቢት 20/2014 /ኢዜአ/ የምርምር ተቋማት የሚሰሯቸው ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ሥራዎች የአሰራር ሥነ-ምግባር መርሆዎችን የተከተሉ መሆን እንደሚገባቸው የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

የትምርት ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት ”የምርምር ሥነ-ምግባር” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ  ከተለያዩ ተቋማት ከተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ የአገሪቱን ያላትን ያላትን ኃብት መጠቀምና ማሳደግ የሚቻለው ችግር ፈቺ የምርምሮችን መሥራት ሲቻል ነው ብለዋል።

ምርምሮቹ በሰዎች፣ በእንስሳት እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ጉዳት እንዳያስከትሉ ለማድረግም ምርምሮቹ የሥነ-ምግባር መርህ የተከተሉ መሆን እንዳለበትም ተናግረዋል።

አንድ የምርምር ሥራ ውጤት ለችግሮች ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ይዞ እንዲመጣ ከተፈለገ ዘርፉን የሚመሩት ተቋማት በአግባቡ መምራት ያስፈልጋል ሲሉም አሳስበዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር የሳይንስና ምርምር ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል ዶክተር ሰለሞን ቢኖር ብሔራዊ  የምርምር ሥነ-ምግባር ኮሚቴ ማቋቋም የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

የሕግ ማዕቀፉ አሁን ላይ ለዩኒቨርሲቲዎች፣ ለምርምር ተቋማትና ለኅብረተሰብ ጤና ተቋማት ተደራሽ እንደሚደረግ አንስተዋል።

በቀጣይም ሚኒስቴሩ ብሔራዊ የኢትዮጵያ የምርምር ሥነ-ምግባር ማኅበራት በተለያዩ ደረጃዎች እንዲመሰረቱ የማድረግና ያሉትን የማጠናከር ሥራ መሥራት እንዲቻል ምክክር መድረኩ ተዘጋጅቷል ብለዋል።

በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ታፈሰ ማቴዎስ ትክክለኛና ውጤታማ የሆነ የምርምር ሥራ ለመሥራት ሥነ-ምግባር መላበስን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

በዚህም የምርምር ሥራ በትክክለኛው መንገድ እንዲሰራ ከዚህ ቀደም ጅምር ሥራዎች  ቢኖሩም ወጥ የሆነ ተቋማዊ አሰራር አለመዘርጋቱ ክፍተት ሆኖ ቆይቷል ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ምትኬ ሞላ በበኩላቸው፤ ለአገሪቷ እድገት መሰረት የሚሆኑ ሥራዎችን ለመሥራት ተመራማሪዎች ተገቢውን የአሰራር ሥነ-ምግባር ሊላበሱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም