የኢትዮጵያን ጠንካራ አንድነት ለመመለስ ፓርቲዎች ልዩነታቸውን አቻችለው በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ጠንካራ አንድነት ለመመለስ ፓርቲዎች ልዩነታቸውን አቻችለው በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ
ባህርዳር ነሀሴ 29/2010 የኢትዮጵያን ጠንካራ አንድነት ለመመለስ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነታቸውን አቻችለው በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ በባህርዳር ከተማ አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ የተናገሩት ለአርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ትናነት በባህርዳርና አካባቢው ነዋሪ ህዝብ አቀባበል ለማድረግ በተዘጋጀ ስነስርዓት ወቅት ነው፡፡ በአቀባበሉ ስርዓት ከጎንደር ከተማ የመጡት አባት አርበኛ ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ መንግስቱ ለኢዜአ እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት ለሀገር አንድነትና ዕድገት የሚቆረቆሩና የሚያስቡ ትውልዶች እየተፈጠሩ ነው። የፖለቲካ ሽኩቻ ለኢትዮጵያ የማይጠቅም መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች በውል ተረድተው ልዩነታቸውን አቻችለው በጋራ ሊሰሩ ይገባል፡፡ "መንግስትም በውጭ ይኖሩ የነበሩና ወደ ሀገር እየገቡ ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን አስማምቶና መብቶቻቸውን ጠብቆ ሀገሪቱን በአንድነት እንዲያለሙና ህዝቡን እንዲደግፉ ማገዝ አለበት" ብለዋል። አዲሱን ትውልድም እንደ አዲስ ቡቃያ ኮትኩቶ በማሳደግ ፍሬ እንዲያፈራ መንግስት ህዝብ የሰጠውን አደራ ለመወጣት ከአድሎ በፀዳ መንገድ ለአንድ ኢትዮጵያ እንዲሰራ መክረዋል። "መንግስት ያመቻቸውን ለውጥ ተከትሎ በውጭ የሚኖሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደሀገር በመግባታቸው ተቀራርበው ለህዝቡ ጥቅምና ለሀገሪቱ ዕድገት የሚበጀውን እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል" ያለው ደግሞ የባህርዳር ከተማ ነዋሪ ወጣት ሰሎሞን ውበት ነው። የተፎካካሪ ፓርቲዎችም ያለፈውን ቂም በመርሳት ለህዝቡና ለሀገሪቱ አንድነት መፍትሄ ይሆናል የሚሉትን ተቀራርበው መስራት እንደሚኖርባቸውም ጠቁሟል፡፡ ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ ወጣት ጌታቸው መላክ እንዳለው የተሰጠውን የምህረት አዋጅ ተከትሎ በስደት የሚኖሩ አክቲቪስቶችና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደሀገራቸው መግባታቸው ለሀገሪቱ ዕድገት ወሳኝ ድርሻ አለው። "ለውጡን ተከትሎ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የስርዓት አልበኝነት አዝማሚያዎችን የተገኘውን ለውጥ እንዳይቀለብሱት ህዝቡም ሆነ ወጣቱ በስሜት ሳይነዳ ሰላሙን ማስጠበቅ አለበት" ብሏል። ወጣት ያየህይራድ የቆየ በበኩሉ " ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገሪቱ በተፈጠረው ሁኔታ ጥሩ የሰላም አየር እንድንተነፍስና መልካም ነገር ለሀገር እድገት እንድናስብ አድርጎናል" ብሏል። ታማኝ በየነ ታግሎ ህዝብን ያታገለ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ መሆኑን የገለጸችው ደግሞ ወጣት ህሊና ታደሰ ናት፡፡ ሀገሪቱ ወደቀደመ ጠንካራ አንድነቷ እንድትመለስና ዕድገቷ እንዲፋጠን ሁሉም በጋራ ሊሰራ እንደሚገባም አሳስባለች።