በምስራቅ አማራ ለሚገኙ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች በቂ መድኃኒት እየቀረበ ነው-የመድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ አማራ ለሚገኙ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች በቂ መድኃኒት እየቀረበ ነው-የመድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት
መጋቢት 20 /2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት ደሴ ቅርንጫፍ በምስራቅ አማራ ለሚገኙ 19 ሆስፒታሎችና 138 ጤና ጣቢያዎች በቂ መድኃኒት እያቀረበ መሆኑን ገለጸ።
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን የደሴ ከተማን ከወረረ በኋላ ዘረፋና ውድመት ከፈጸመባቸው የጤና ተቋማት መካከል መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት መጋዘን ዋናው ሲሆን ከቅርንጫፍ መጋዘኑ ብቻ ከ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ዘረፋና ውድመት መድረሱ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት ደሴ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ እሸቴ ሹሜ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የተቋሙ ውድመት ከገንዘብ በላይ በማኅበረሰቡ ጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሮ ነበር።
በዘረፋና ውድመቱ የፖሊዮ ክትባት፣ የኤች.አይ.ቪ ኤድስ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ቁሳቁሶችና ክትባት፣ የደም ግፊትና መሰል መድኃኒቶች ሜዳ ላይ ተጥለው እንደነበር የገለጹት ሃላፊው ሁኔታው ለህጻናት ጨምሮ ለአካባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ የጤና ጠንቅ ሊያስከትል የሚችል እንደነበረም አስታውሰዋል።
ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቱ ከደረሰበት ውድመት ወጥቶ የሕክምና ተቋማት የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በቂ መድኃኒት ማሰራጨት ጀምሯል ነው ያሉት።
የአጋሮችን ትብብር በመጠቀም ከጥር ወር ጀምሮ ክትባት እንዲሰጥ፣ የፀረ- ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መድኃኒቶችን ደግሞ መሰጠት እንዲጀምሩ ተደርጓል ነው ያሉት።
በዚህም በምስራቅ አማራ የሚገኙ 138 ጤና ጣቢያዎች፣ 19 ሆስፒታሎች እና የግል ጤና ተቋማት በቂ መድኃኒት አግኝተው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ መደረጉን ነው የገለጹት።