ኢትዮጵያ ያሏትን በርካታ ባህሎችና የቱሪዝም መስህቦች ይበልጥ ለዓለም ማስተዋወቅ አለባት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ያሏትን በርካታ ባህሎችና የቱሪዝም መስህቦች ይበልጥ ለዓለም ማስተዋወቅ አለባት
አዲስ አበባ መጋቢት 20/2014 /ኢዜአ/ ኢትዮጵያ ያሏትን በርካታ ባህሎችና የቱሪዝም መስህቦች ይበልጥ ለዓለም ማስተዋወቅ አለባት ሲሉ በሻሸመኔ የሚኖሩ የጃማይካ ተወላጆች (የራስ-ተፈሪያን ማኅበረሰብ አባላት) ተናገሩ።
የራስ-ተፈሪያን ማኅበረሰብ አባላት በሻሸመኔ ለሦስት ቀናት በተካሄደው የኦሮሚያ የባህል ሣምንት በትላንትናው ዕለት ተሳትፈዋል።
እነዚህ የራስ-ተፈሪያን የማኅበረሰብ አባላት ኢትዮጵያ የባህል ብዝኃነት ያላት ታሪካዊና ጥንታዊ አገር በመሆኗ ይህንን ባህል ለዓለም ማስተዋወቅ ይገበታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ በርካታ ባህሎች የአንድነትና የውበት ምንጭ በመሆኑ ከዚህ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የቱሪስት መስህብ እንዲሆን ሊሰራበት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ከ80 በላይ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መኖራቸውን ጠቁመው ይህም በአገሪቱ ሊተዋወቁ የሚችሉ በርካታ ባህል መኖሩን ያሳያል ነው ያሉት።
ባህላዊ እሴቶችን እንዲጎለብቱ እንዲህ ያሉ የባህል ፌስቲቫሎች መጠናከር እንዳለባቸው ገልጸው ፌስቲቫሎች ባህልን በቀላሉ አውጥቶ ለማሳየት እድል ይፈጥራል ብለዋል።
ከአስተያየጥ ሰጪዎቹ መካከል ፌውሌን ኤኪንስ እንደገለፁት ኢትዮጵያ ለቱሪስት መስዕብ የሚሆን ውብ ባህል ያላት አገር በመሆንዋ ይህን ለቀጣዩ ትውልድ ጠብቆ ማቆየት ይገባል፡፡
ቸከሚሎ በበኩላቸው ሰዎች ጥበባቸውን ለአንድነት እንጂ ለልዩነት ሊጠቀሙት አይገባም፤ እንዲሁ መቀጠል አለበት፤ ይስ ፌስቲቫል የበለጠ አንድ የሆነች ኢትዮጵያ ማሳያ ነው ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ያሏትን ባህላዊ እሴቶች አስጠብቃ ለመቆየት አገራዊ አንድነቷን ማጠናከር እንደሚገባና ለዚህም ሁሉም መረባረብ እንደሚገባው ምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል።