ቀጥታ፡

ቦርዱ ለሥራ ማስኬጃ የሚውል 50 ሚሊዮን ብር ለፖለቲካ ፓርቲዎች ሊያከፋፍል ነው

መጋቢት 20/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሥራ ማስኬጃ የሚውል 50 ሚሊዮን ብር ለፖለቲካ ፓርቲዎች ሊያከፋፍል ነው።

ይህ የተገለጸው ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እያካሄደበት ባለበት ወቅት ነው።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት በአዲሱ የምርጫና የፖለቲካ ፖርቲዎች አዋጅ 1162 መንግሥት ለፖለቲካ ፓርቲዎች በቋሚነት የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግ መጠቀሱን ገልጸዋል።

በዚህ መሠረት ምርጫ ቦርዱ ለዚህ ዓመት ከመንግሥት 230 ሚሊዮን ብር ለማግኘት ጠይቆ አገሪቷ ካለችበት ወቅታዊ ችግር ምክንያት ገንዘቡ እንደማይሰጥ እንደተገለጸላቸው ተናግረዋል።

ሆኖም ምርጫ ቦርዱ ባለፈው የምርጫ ወቅት ከወረቀት ህትመት የተረፈውን 50 ሚሊዮን ብር ለፓርቲዎች ለማከፋፈል ከመንግሥት ፈቃድ ማግኘቱን ገልጸዋል።

ይህም ገንዘብ 30 በመቶ ለአገራዊ ፖርቲዎች፣ 20 በመቶው ለክልላዊ ፓርቲዎች እንዲሁም በፓርቲዎች የሴትና የአካል ጉዳተኞች አመራሮች ብዛት ታይቶ የሚከፋፍል መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የፓርቲዎች ከዚህ ቀደም የነበራቸው የገንዘብ አጠቃቀምና የኦዲት ሪፖርትም ግንዛቤ ውስጥ የሚገባ መሆኑንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም