ቀጥታ፡

የህዝብ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የሚጠበቅብንን ሃላፊነት እንወጣለን-የምክር ቤት አባላት

ሶዶ፤ መጋቢት 20/2014(ኢዜአ)፡ የህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እንደሚወጡ የወላይታ ዞን ምክር ቤት አባላት አስታወቁ።

ኢዜአ እንደ ሀገር ከሰሞኑ የተካሄደውን ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተከትሎ ከምክር ቤቱ አባላት ጋር ቆይታ አድርጓል ።

የምክር ቤቱአባላት፣"የልማትም ሆነ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲመለሱ ለማድረግ  ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እንሰራለን" ብለዋል።


የምክር ቤት አባሏወይዘሮ አለሚቱ ባልቻ  እንደገለጹት ሰሞኑን በተካሄደው ህዝባዊ ውይይት ከሙስናና ብልሹ አሰራር ጋር ተያይዞ የተነሱ ችግሮችን አስፈፃሚ አካላት እንዲቀርፉ የክትትልና የድጋፍ ስራ ይሰራል።

"በተለያዩ ተቋማት የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለቶችን ለማስቀረት የአሰራር ማዕቀፍ እንዲበጅና የተጠያቂነት መርህ ተግባራዊ እንዲደረግ እንሰራለን" ብለዋል።

የህዝቡን ችግሮች ቁጭ ብሎ ለማዳመጥ የሚያስችል እድል በመመቻቸቱ ህብረተሰቡ የታዘባቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ነቅሶ በማውጣት እንዲፈቱለት መጠየቁን ያስረዱት ወይዘሮ አለሚቱ፤በየደረጃው የሚገኙ አስፈጻሚ አካላት   የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ታደሰ ኦሎሎ በበኩላቸው የኑሮ ውድነት ችግርን በተወሰነ መልኩ ለመፍታት ታስቦ የተጀመረው የእሑድ ገበያና መሰል የመፍትሄ እርምጃዎችን  ወደ ሁሉም ወረዳዎች በማውረድ ገበያውን ማረጋጋት እንዲቻል ግፊት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በግንባታ ሂደት ላይ ያለውን የመርካቶ ገበያ በቅርቡ ለማጠናቀቅ በተገባው ቃል መሰረት ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት እንዲጀምር ያልተቋረጠ ክትትልና ድጋፍ  እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

የመልማትምሆነሌሎችየመብት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ የሰላም መኖር አስፈላጊ መሆኑን ያመለከቱት የምክር ቤት አባል፤  ህዝቡ ሰላሙን ለማረጋገጥ ከወትሮ በተለየ መልኩ በትብብር ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ህገ ወጥ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን በማጋለጥ ተባባሪነቱን በተግባር ሊያረጋግጥ እንደሚገባ  አስገንዝበዋል።

በህዝብ ዘንድ በየጊዜው የቅሬታ ምንጭ የሚሆኑ ችግሮች ክትትል በማድረግና በመለየት ምላሽ እንዲያገኙ የተጣለባቸውን አደራ ለመወጣት እንደሚሰሩ የተናገሩት ደግሞ የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ በላይነሽ ወንድሙ ናቸው።

በትራንስፖርት፣በትምህርትና በሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ካለ በቂ ምክንያት ዋጋ እየጨመሩ የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስና በህዝብ ላይ ጫና እንዲበረታ በሚያደርጉ አካላት ላይ ክትትል በማድረግ እርምጃ እንዲወሰድ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ከውሃና ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ውስንነቶች መሻሻል እንዲችሉ በተቀናጀ መልኩ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች መቅረፍ እንዲቻል አስፈፃሚ አካላትን በመከታተልና በመተባበር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም