ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ በማድረግ ሊከናወኑ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ በማድረግ ሊከናወኑ ይገባል
መጋቢት 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የፖለቲካዊና ማኅበራዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚከናወኑ እንቅስቃሴዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ በማድረግ ሊካሄዱ እንደሚገባ ተገለጸ።
የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል “ሐይማኖትና መንግሥት መነጣጠል “ እና “የህዳጣን እና ተጋላጭ ህብረተሰብ ክፍሎች አካላት ጉዳይ” በሚል ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተጋበዙ ወጣት ምሁራን ጋር የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው።
በዚህ ወቅት ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ድባቤ ባጫ "በአካል ጉዳተኞች ላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መገለሎች ይስተዋላሉ" ብለዋል።
እነዚህ መገለሎች በትምህርት ቤት፣ በጤና ተቋማት፣ በመሠረተ ልማቶችና በትራንስፖርት ዘርፉ በጉልህነት ይታያሉ ያሉት ወይዘሮ ድባቤ ችግሮቹን ለመፍታት አካታች የሆኑ የፖሊሲ ቀረጻዎችና ተግባራት ሊከናወኑ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በተለይም በኢትዮጵያ የፖለቲካዊና ማኅበራዊ ችግሮችን ለመፍታት በሚከናወኑ እንቅስቃሴዎች ላይ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ ተግባራት ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ሲሉ ነው የገለጹት።
"በኢትዮጵያ የሚገኙ 20 ሚሊዮን ገደማ አካል ጉዳተኛ የህብረተሰብ ክፍሎችን ሳናካትት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን ልናሳካና ልናቅድ አንችልም" ብለዋል።
የሚዲያ ተቋማትም በዚህ ረገድ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ መርሐግብሮችን ሊቀርጹ ይገባል ሲሉ አመልክተዋል።
በመድረኩ ላይ የሐይማኖትና መንግሥት መነጣጠል እና የህዳጣንና ተጋላጭ ህብረተሰብ ክፍሎች አካላት ጉዳይ በሚል ርዕስ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ነው።