አሸባሪው ህወሓት ለጦርነት አስገድዶ እየመለመለ በመሆኑ ሸሽተን ወደ አማራ ክልል መጥተናል - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሓት ለጦርነት አስገድዶ እየመለመለ በመሆኑ ሸሽተን ወደ አማራ ክልል መጥተናል
መጋቢት 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት ለጦርነት አስገድዶ እየመለመለ በመሆኑ ወደ አማራ ክልል በሽሽት መምጣታቸውን የትግራይ ክልል ተፈናቃዮች ተናገሩ።
አሸባሪው ቡድን ወደ ትግራይ የሚገባውን የእርዳታ እህል ለህዝቡ ተደራሽ ከማድረግ ይልቅ ለውጊያ ለሚያሰለጥነው ኃይል እያዋለ መሆኑንም ገልጸዋል።
"ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል እገባለሁ" ብሎ የተነሳው ቡድን በተለይም የትግራይን ህዝብ ለከፍተኛ ችግርና ስቃይ ዳርጎ ዓላማውን ለማሳካት እየሰራ ይገኛል።
ለዓላማው ማስፈጸሚያ ደግሞ እድሜና ፆታ ሳይለይ በአስገዳጅ ሁኔታ ለጦርነት እየመለመለ የጥፋት ዝግጅቱን አለማቋረጡን ከትግራይ ክልል ወደ አማራ ክልል የሸሹ ወጣቶች ለኢዜአ ተናግረዋል።
አሸባሪው ህወሓት እየፈጸመ ባለው ግፍ የክልሉ ነዋሪዎች በእጅጉ እየተማረሩና በተገኘው አጋጣሚ አካባቢውን ለመልቀቅ የሚጥሩ እንዳሉ ገልጸዋል።
ለዚህም እኛ ማሳያ ነን የሚሉት ወጣቶቹ በአስገዳጅነት ወደ ጦርነት ለማስገባት ከሚያደርገው ምልመላ አምልጠን ወደ አማራ ክልል ለመግባት ችለናል ብለዋል።
የእርዳታ ቁሳቁስና የምግብ እህል ወደ ትግራይ ክልል ሲገባ አሸባሪው ህወሃት ተደራሽ የሚያደርገው ለጦርነት ለሚያሰለጥነው ኃይል እንጂ በችግር ላይ ለሚገኘው ህዝብ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።
ከትግራይ ወደ አማራ ክልል ስንገባ የአማራ ልዩ ኃይል እና መከላከያ ሰራዊት ተቀብለውን በጥሩ ሁኔታ ላይ እንገኛለን ብለዋል።
የሰሜን፣ ደቡብ ወሎና ከሚሴ ሀገረስብከት ሊቀ-ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ፤ የሰሜንና ደቡብ ወሎ ህዝብ በጥፋት ቡድኖች ብዙ መከራና ግፍ ደርሶበት ማሳለፉን ይናገራሉ።
በጦርነቱ የትግራይ ክልል ህዝብን የማይወክሉ የጥፋት ቡድኖች በአማራ ክልል በወረራ በቆዩባቸው አካባቢዎች ከሊቅ እስከ ደቂቅ ከገጠር እስከ ከተማ ዘረፋና ውድመት መፈጸማቸውን ገልጸዋል።
እነዚህ የጥፋት ኃይሎች ከትግራይ ህዝብ የተለዩ መሆናቸውን ሁላችንም ስለምንገነዘብ የተፈናቀሉትን በመቀበል የቻልነውን ሁሉ እገዛ በማድረግ ላይ እንገኛለን ብለዋል።
የአካባቢው ህዝብ በደረሰበት በደል ቂም ሳይቋጥር በችግርም ላይ ሆኖ ወገኖቹን እየተቀበለ መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ