በባህር ትራንስፖርትና የገቢ እቃዎች ማጓጓዝ ላይ ለተፈጠረው ጫና አማራጮች እየተፈለጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በባህር ትራንስፖርትና የገቢ እቃዎች ማጓጓዝ ላይ ለተፈጠረው ጫና አማራጮች እየተፈለጉ ነው
መጋቢት 20/2014/ኢዜአ/ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና የገቢ እቃዎች ማጓጓዝ ላይ ለተፈጠረው ጫና አማራጮች እየተፈለጉ መሆኑን የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ገለጸ።
የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ አንድ ወር አልፎታል፤ ጦርነቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫናዎችንም አሳድሯል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ካሳደረው ጫና በማገገም ላይ የነበረው የዓለም የንግድ መዛባት አሁን ላይ በጦርነቱ ምክንያት ለሌላ ቀውስ ተዳርጓል።
በተለይም የምግብ፣ የነዳጅ፣ የዘይትና ሌሎችም ምርቶች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቶባቸዋል።
የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በተለይም የባህር ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ከፍ ያለ ጉዳት ማስከተሉ እየተነገረ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የባህር ትራንስፖርት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ወንድወሰን ካሳ፤ በዚሁ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
የሁለቱ አገሮች ጦርነት ለዘርፉ ከባድ ፈተና ደቅኗል ያሉት አቶ ወንድወሰን፤ የኢትዮጵያ መርከቦች የአገልግሎት ወጪ እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም የነዳጅ ወጪያቸው ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ የ42 በመቶ ጭማሪ ሊያስከትል እንደሚችል ተናግረዋል።
የጦርነቱ ተፋላሚ አገራት የአውሮፓና የኤዥያ መተላለፊያ በመሆናቸው በተለይም በባቡር ለሚጓጓዙ ምርቶች ከፍተኛ ችግር ሆኗል ብለዋል።
በ2021 እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ኮንቴይነሮች በባቡር መጓጓዛቸውን ገልጸው፤ በዚህ ዓመት የሚቋረጥ ከሆነ ከ5 እስከ 8 በመቶ እቃዎች ወደ ባህር ትራንስፖርት ሊመጡና ጫና ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ገልጸዋል።
በመሆኑም ጦርነቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የባህር ትራንስፖርት እጥረትና በባህር በሚጓጓዙ እቃዎች ላይ የጭነት የዋጋ ጭማሪ ሊያስከትል ይችላል ነው ያሉት።
የሁለቱ አገሮች ጦርነት እልባት ካላገኘ በባህር ትራንስፖርቱ ላይ የሚፈጥረው ጫና ተባብሶ ሊቀጥል እንደሚችልም ተናግረዋል።
የወደቦችና የባህር ትራንስፖርት መሰረተ ልማቶች ሊወድሙ ስለሚችሉ ወደ ተለመደው እንቅስቃሴ በፍጥነት መግባት ሊያስቸግር እንደሚችል ጠቁመዋል።
በመሆኑም የባህር ትራንስፖርቱ አሁን ካለበት ጫና ይበልጥ ወደ ከፋ ችግር እንዳይሸጋገር ለሚገቡ ምርቶች አማራጭ መንገዶችን መፈለግ ይገባል ብለዋል።
ከጥቁር ባህር አካባቢ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩ አማራጮች በሌሎች አገራት መኖራቸውን የተናገሩት ምክትል ሥራ አስፈጻሚው ከኦማን የብረት ምርት በማስገባት ላይ እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል።
ከህንድም ብረትና የስንዴ ምርት አማራጭ መኖሩን ጠቅሰው፤ ካናዳና አርጀንቲናም የስንዴ አምራች በመሆናቸው አማራጮችን ማየት ይጠቅማል ብለዋል።
የሱፍ ዘይት በጦርነቱ ምክንያት ምርቱ ወደ ገበያ ባይቀርብም ከኢንዶኔዥያና ማሌዥያ የፓልም ዘይትንና በተወሰነ ደረጃም የሱፍ ዘይትን ማስገባት ይቻላል ብለዋል።