ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያቀረቧቸውን አቤቱታዎች እልባት ለመስጠት እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያቀረቧቸውን አቤቱታዎች እልባት ለመስጠት እየሰራ ነው
መጋቢት 20/2014/ኢዜአ/ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያቀረቧቸውን አቤቱታዎች የምርመራ ቡድን በማደራጀት እልባት ለመስጠት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለጸ።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እያካሄደ ነው።
በዚህም ተጥሎ ከነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋርና በሌሎች ጊዜያቶች ተፈጽመውብናል ብለው ፓርቲዎች ላቀረቧቸው አቤቱታዎች የምርመራ ቡድን በማደራጀት በርካታሥራዎች መሥራቱን ቦርዱ ገልጿል።
ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያቀረቡትን አቤቱታ እንደ መነሻ በመያዝም አቤቱታው የቀረበባቸው ቦታዎች ላይ በመንቀሳቀስና ምርመራ በማድረግ ሕጋዊ መፍትሔ እንዲኖረው ማድረጉም በሪፖርቱ ቀርቧል።
በዚህም በኦነግና ኦፌኮ ፓርቲዎች በኩል የተነሱትን አቤቱታዎች በመያዝ ቦታዎቹ ድረስ በመሄድ ምርመራ ማከናወኑን ገልጾ፤ ሕጋዊ አሰራር እንዲተገበር ውሳኔ አስተላልፎ መፍትሄ ማሰጠቱን አንስቷል።
ቀጣይ በምርመራ ላይ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አቤቱታዎችን እልባት እንዲያገኙ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
በውይይቱ በመሳተፍ ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ፖርቲዎችም ቦርዱ እያከናወነ ያለውን ተግባርም አድንቀዋል።
መንግሥት ዘንድሮ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ፣ ጠቅላላ ጉባዔ ያደረጉ ፓርቲዎች ተሞክሮና ቀጣይ የሚያደርጉ ፓርቲዎች አካሄድ በሚሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።