የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ በልዩ ትኩረት እንዲሰራ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ በልዩ ትኩረት እንዲሰራ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ
መጋቢት 19/2014(ኢዜአየኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ በልዩ ትኩረት እንዲሰራ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሰረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በመገኘት እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችንና አገልግሎት አሰጣጡን በተመለከተ ቋሚ ኮሚቴው ተዘዋውሮ ተመልክቷል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ተቋሙ ትልቅ አገራዊ ራእይ ያለው ተቋም መሆኑን መመልከታቸውን ገልጸዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ፤ በቴክኖሎጂ የዘመኑ አገልግሎቶችን በመስጠት ተቋሙ ለሌሎችም አርአያ የሚሆኑ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
የሥራ አካባቢን ምቹ በማድረግ ረገድም የመንገዶች አስተዳደር የጀመራቸው አበረታች ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።
የፕሮጀክቶች መጓተት፣ ከካሳ ክፍያ ጋር የሚቀርቡ ቅሬታዎች እንዲሁም ከጨረታ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ይሻሉ ብለዋል ሰብሳቢዋ።
በተለይም የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በልዩ ትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ፤ ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ 129 የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በፕሮጀክቶቹ ግንባታ ሂደት አገራዊ ሁኔታ፣ የገበያ መዋዥቅ እንዲሁም የተጋነነ የወሰን ካሳ ክፍያ ፈታኝ ችግሮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በጦርነት ምክንያት አሸባሪው ህወሓት በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች በፕሮጀክቶች ላይ ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ዘረፋና ውድመት መፈፀሙንም አስታውሰዋል።
በዚህም ከ7 ቢሊየን ብር በላይ ካሳ የሚያስፈልጋቸው የግንባታ ተቋራጮች ስለመኖራቸው ጠቅሰዋል።
ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ሊሰራ ይገባል ብሏል ቋሚ ኮሚቴው።