ቀጥታ፡

የወንዶች የቮሊቦል ጥሎ ማለፍ ውድድር አምስተኛ ቀን ውሎ

መጋቢት 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) የ2014 ዓ.ም የወንዶች ጥሎ ማለፍ ውድድር ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች ብሔራዊ አልኮልና አረቄና መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ተጋጣሚዎቻውን አሸንፈዋል።

ከመጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም እየተካሄደ ያለው ውድድር ዛሬ በአምስተኛ ቀን ውሎው ሁለት ጨዋታዎች ተካሄደዋል።

ብሔራዊ አልኮልና አረቄ አዲስ አበባ ፖሊስን 3 ለ 1 ሲያሸንፍ፤መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ መከላከያን 3 ለ 0 ረቷል።

ውጤቱንም ተከትሎ ብሔራዊ አልኮልና አረቄና መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ በውድድሩ ሁለተኛ ድላቸውን ያስመዘገቡ ሲሆን፤በአንጻሩ መከላከያ እስካሁን ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዷል።

አዲስ አበባ ፖሊስ በውድድሩ ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ መከላከያን 3 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

የጥሎ ማለፍ ውድድሩ ቀጣይ ጨዋታዎች ነገም ቀጥለው የሚካሄዱ ሲሆን፤ከጠዋቱ 2 ሰአት ከ30 ሙገር ሲሚንቶ ከመከላከያ እንዲሁም አዲስ አበባ ፖሊስ ከመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከረፋዱ 4 ሰአት ላይ ይጫወታሉ።

እ.አ.አ በ2023 የአፍሪካ የወንዶች ክለቦች የቮሊቦል ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክል ክለብ መምረጥና የፕሪሚየር ሊግ ክለቦችን የውድድር አማራጭ ማስፋት ታሳቢ በማድረግ ውድድሩ እየተካሄደ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን ገልጿል።

ወላይታ ዲቻና ባህርዳር ከተማ “ምክንያታቸውን በግልጽ ሳያሳውቁ ከአቅም በላይ ችግር ገጥሞናል” በሚል በውድድሩ ላይ እንዳልተሳተፉ ፌዴሬሽኑ ለኢዜአ መግለጹ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ የወንዶች የቮሊቦል ጥሎ ማለፍ ውድድር መጋቢት 22 ቀን 2014 ዓ.ም ይጠናቀቃል።

በተያያዘ ዜና ትናንት በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም በተደረገ የኢትዮጵያ የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታዎች ወላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ ጌታዘሩ ስፖርት ክለብን 3 ለ 1 አሸንፏል።

መጋቢት 24 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከጌታዘሩ ስፖርት ክለብ ጋር ከጠዋቱ 2 ሰአት ከ30 በሚያደርጉት ጨዋታ የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ዙር እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን አስታውቋል።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በ12 ነጥብ ሲመራ፤ብሔራዊ አልኮልና አረቄ በስምንት ነጥብ ሁለተኛ ፌደራል ማረሚያ ቤቶች በሰባት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም