ቀጥታ፡

51ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር በሐዋሳ ተጀመረ

መጋቢት 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) 51ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር በሐዋሳ ከተማ ተጀመረ ።

የሻምፒዮናውን ውድድር የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ በተገኙበት ነው በሐዋሳ ስቴዲየም በይፋ የተጀመረው።

በዕለቱ የሴቶች አሎሎ ውርወራ፣ የወንዶች ሱሉስ ዝላይ ፍፃሜ ውድድር የተካሄደ ሲሆን የወንዶች 10 ሺህ ሜትር የፍፃሜ ውድድርም ይጠበቃል።

አትሌት ዙርጋ ኡስማን ከመከላከያ በሴቶች የአሎሎ ውርወራ አሸናፊ ሆና የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሆናለች።

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መርሃዊት ፀጋዬ፤ ከመከላከያ አመለ ይበልጣል ደግሞ ሁለተኛ እና ሶስተኛ በመሆን የብርና የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊዎች ሆነዋል።

በስሉስ ዝላይ አትሌት ክችማን ኡጅሉ ከኢትዮጵያ ኤሌትሪክ የወርቅ፣  ዶል ማች  ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብር እንዲሁም በቀለ ጅሎ ከኦሮሚያ ክልል የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊዎች ሆነዋል።

በተመሳሳይ በሁለቱም ፆታዎች የ800፣  የ400 እና የ100 ሜትር የማጣሪያ የሩጫ ውድድሮች ተከናውነዋል።

በ1963 ዓ.ም የተጀመረው የኢትዮጵያ አትሌቲከስ ሻምፒዮና ፌዴሬሽኑ ከሚያዘጋጃቸው ውድድርች ከፍተኛውን ግምት የሚሰጠው ሲሆን  ባሳለፍነው ዓመት 50 ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓሉን ማክበሩ ይታወሳል።

50ኛው የኢትዮጵየ አትሌቲክስ ሻምፒዮናም በአዲስ ዓበባ ከተማ ነበር የተካሄደው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም