የደም ለጋሾች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን ተከትሎ ኅብረተሰቡ ደም በመደበኛነት እንዲለግስ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የደም ለጋሾች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን ተከትሎ ኅብረተሰቡ ደም በመደበኛነት እንዲለግስ ተጠየቀ
መጋቢት 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) የደም ለጋሾች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን ተከትሎ ኅብረተሰቡ ደም በመደበኛነት እንዲለግስ የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ ጥሪ አቀረበ።
የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ ከዚህ ቀደም በቀን ይሰበሰብ ከነበረው ከ300 እስከ 400 ከረጢት ደም አሁን ላይ ከ200 ዩኒት በታች መድረሱን ገልጿል።
በባንኩ ደም ለጋሾች ዘርፍ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ተመስገን አበጀ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከደም ለጋሾች የሚሰበሰበው የደም መጠን እየቀነሰ መጥቷል።
በአንዳንድ ክልሎች የደም እጥረት መኖሩን ገልጸው፤ በአዲስ አበባ ከሚሰበሰበው የደም መጠን እስከ 40 በመቶ ለክልሎች እየተላከ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም በሶማሌ፣ በኦሮሚያ፣ ሀረርና በደቡብ ክልሎች ባሉ የደም ባንኮች በቂ ደም አለመኖሩንና አሁን ላይ ከአዲስ አበባ ደም እየተላከላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም እስከ መጋቢት/2014 ዓ.ም ድረስ ከ2 ሺህ 300 በላይ ከረጢት ደም ወደ ክልሎች መሰራጨቱን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ የካንሰርና የደም ካንሰር ታካሚዎች እንዲሁም በወሊድ ምክንያት ደም የሚፈሳቸው እናቶች ቁጥር መጨመር ሌላኛው ጫና መሆኑን አብራርተዋል።
ይህ ደግሞ በደም ፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለመመጣጠን ችግር እንዲፈጠር ማድረጉን ጠቁመዋል።
አሁን ላይ የገጠመው የደም ለጋሽ እጥረት ከፋሲካ ጾም ጋር በተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠው፤ ይህም ችግር የረመዳን ጾም ሲገባ ሊጨምር እንደሚችል ስጋታቸውን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ኅብረተሰቡ በመደበኛነት ደም በመለገስ የወገኑን ሕይወት መታደግ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።
የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ በ2013 ዓ.ም 288 ሺህ ከረጢት ደም መሰብሰብ መቻሉን ገልጿል።