ቀጥታ፡

ዓለም ዓቀፍ የሎጂስቲክ ኩባንያዎች ከ49 በመቶ ያልበለጠ ድርሻ ይዘው ከአገር ውስጥ ኩባንያዎች ጋር በሽርክና እንዲሰሩ ተወሰነ

አዲስ አበባ ነሀሴ 29/2010 ዓለም ዓቀፍ የሎጂስቲክ ኩባንያዎች ከ49 በመቶ ያልበለጠ ድርሻ ይዘው ከአገር ውስጥ ኩባንያዎች ጋር በሽርክና እንዲሰሩ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ ውሳኔ አሳልፏል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለኢዜአ በላከው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከተው፤ በዘርፉ የውጭ ባለሃብቶች ተሳትፎ በመገደቡ የገቢና ወጭ ስራ ላይ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ማግኘት አልቻሉም። በመሆኑም ቦርዱ በተሰጠው ስልጣን መሰረት፣ ለአገር ውስጥ ባለሃብቶች ብቻ ተከልሎ የነበረው ዕቃዎችን የማሸግ፣ የማስተላለፍ እና የመርከብ ውክልና አገልግሎቶችን በመስጠት የኢንቨስትመንት መስክ አለም አቀፍ የሎጂስቲክስ ኩባንያዎች አናሳ ድርሻ ይዘው ከአገር ውስጥ የሎጂስቲክስ ኩባንያዎች ጋር በሽርክና አብረው መስራት እንዲችሉ ውሳኔ አስተላልፏል። በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የአምራቹን ዘርፍ ዕድገት ለማፋጠን የሎጂስቲክስና የጉምሩክ አሰራሮችን ለማሻሻል ሙከራ ቢኖርም ይህ ነው የሚባል ለውጥ ሊመጣ እንዳልቻለ ተጠቁሟል። በኢትዮጵያ ያለው የሎጂስቲክስ ኢንዱስትሪና የጉምሩክ ስርዓት ከአለም አቀፍ መመዘኛዎች ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ አፈፃፀም ላይ የሚገኝ መሆኑንም መግለጫው አመልክቷል። የብሔራዊ ሎጅስቲክስ ስትራቴጂ በሚንስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት መጽደቁን ያስታወሰው የኮሚሽኑ መግለጫ ዘርፉ ያሉበትን ችግሮች ለመለየትና አቅጣጫ ለመጠቆም ከዓለም ባንክ ተቋም ጋር በመተባበር ጥናት ሲካሄድ መቆየቱ ገልጿል። የተላለፈው ውሳኔ አገሪቱ ቴክኖሎጂ ተኮርና በአለም አቀፍ ደረጃ ተለዋዋጭ ከሆነው የሎጂስቲክስ ኢንዱስትሪ ጋር አብራ እንድትጓዝ ለማድረግ አለም አቀፍ ልምድ ያካበቱ የሎጂስቲክስ ኩባንያዎች ከሃገር ውስጥ የሎጂስቲክስ ኩባንያዎች መስራት የሚያስችላቸው እንደሆነ ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም