ቀጥታ፡

በክልሉ የጸጥታ ችግርን ለመፍታት በተደረገው ጥረት የተገኘው ውጤት ሊበረታታ የሚገባው ነው- አቶ አሻድሊ ሃሰን

አሶሳ፤ መጋቢት 19 / 2014 (ኢዜአ) በክልሉ መተከል፣ ካማሺና አሶሳ ዞኖች እንዲሁም በማኦ ኮሞ ልዩ ወረዳ የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት በተደረገው ጥረት የተገኘው ውጤት ሊበረታታ የሚገባው ነው ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሃሰን አስታወቁ፡፡

የክልሉ ምክር ቤት ሰባተኛ የስራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ በአሶሳ ከተማ  ሲጀመር ርዕሰ መስተዳድሩ ያለፉት ስድስት ወራት የስራ አፈጻጻም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት ፤የክልሉን ሠላም ሙሉ በሙሉ በመመለስ ህግን ለማስከበር መስዋዕትነት እየተከፈለ ነው።

መስዋዕትነቱ ለልማት ውሎ ቢሆን ኖሮ በማህረሰቡ ህይወት ላይ ይገኝ የነበረውን ለውጥ በቁጭት የጠቀሱት አቶ አሻድሊ ሃሰን ሆኖም ለሠላም የተከፈለ ውድ ዋጋ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በመተከል፣ ካማሺና  አሶሳ ዞኖች እንዲሁም በማኦ ኮሞ ልዩ ወረዳ የተከሰተው የጸጥታ ችግር ለመፍታት በተደረገው ጥረት የተገኘው ውጤት  ሊበረታታ የሚገባው ነው ብለዋል።

የካማሺ ዞን ሠላም ለመመለስ በመንግስት እና ህዝብ የተደረገው ጥረት በአሁኑ ወቅት ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ይህም የክልሉ ህብረተሰብ እና መንግስት ችግሩን በዘለቄታው ለመፍታት ያደረጉት ጥረት ተጨባጭ ማሳያም ነው ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡

የአካባቢውን ባህል መሠረት በማድረግ በተከታታይ በተካሄዱ ህዝባዊ ውይይቶች የወረደውን እርቀ ሠላም አቶ አሻድሊ ለምክር ቤቱ ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

ይህም በግጭት ምክንያት ሸሽተው ጨካ የገቡ የማህበረሰብ ክፍሎችን ወደ ከተሞች እንዲሰባሰብ ማስቻሉን ገልጸው፤ ህብረተሰቡ ከጸጥታ ችግር ወጥቶ ወደ ልማቱ እንዲመለስ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በጸጥታ ስጋት ውስጥ ሆኖ በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በከተማ ልማት፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በገቢ ማሰባሰብ፣ በሴቶች እና ህጻናት እና ሌሎችም ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራትን አስመልክቶ ርዕሰ መስተዳድሩ በዝርዝር ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡

ሠላማዊ በሆኑ አካባቢዎች ወጣቶች በማዕድን ዘርፍ እና በግብርና አደራጅቶ ለማሰማራት በተደረገው ጥረት የተገኘውን ውጤት ገልጸው፤ ባለሃብቶችን ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገቡ የተደረገ ጥረት መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖች አቅም በፈቀደ ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ የተደረገውን ርብርብ የጠቀሱት አቶ አሻድሊ፤ በተቋማት እቅድ አፈጻጸም ያጋጠሙ ችግሮችንም ለምክር ቤቱ አንስተዋል፡፡

ለክልሉ ሠላም መደፍረስ ምክንያት በሆነው የሽብርተኛው ህወሃት የጥፋት ተላላኪዎች በሚነዙት የሃሰት ወሬ የአካባቢው ማህበረሰብ ወደ ኋላ ሳይል ሠላምን በመመለሱ ሂደት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተለይ በየደረጃው የሚገኘው አመራር እና ባለሙያ የክልሉን ሠላም በአጭር ጊዜ በዘላቂነት ለመመለስ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሃላፊነትን በላቀ ቁርጠኝት መወጣት ይጠበቅብናል ብለዋል አቶ አሻድሊ፡፡

ጉባኤው እስከ ነገ  እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከአሶሳ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም