ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከጅቡቲ ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌ ጋር ተወያዩ

አዲስ አባባ መጋቢት 19/2014 /ኢዜአ/ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከጅቡቲ ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌ ጋር በሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ።

የጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌ፤ በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወቃል።

ፕሬዝዳንቱ ዛሬ ረፋድ ላይ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና መሥሪያ ቤትን ጎብኝተዋል።

ከጉብኝቱ በኋላም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

ውይይቱን የተከታተሉት የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ፤ ሁለቱ መሪዎች በሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ገልጸዋል።

የሁለቱን አገሮች የመንገድ መሰረት ልማት ይበልጥ ለማሳለጥ የፈጣን መንገድ ግንባታ ለማከናወን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተነጋግረው ተስማምተዋል ነው ያሉት።

ጅቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ በተሻለ መልኩ ተጠቃሚ በምትሆንበት ሁኔታ ተነጋግረው ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል ሚኒስትሩ።

የባቡር መሰረተ ልማቱን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ በጋራ የባቡር ኩባንያው በኩል መሥራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ሁለቱ መሪዎች ተነጋግረዋል።

የሁለቱ መሪዎች ምክክር ከኢትዮጵያ ለጅቡቲ በሚቀርበው የመጠጥ ውሃ፣ የቴሌኮም መሰረተ ልማት እንዲሁም በንግድና ቱሪዝም ዘርፍ ላይ በጋራ ለመሥራት በሚቻልበት ሁኔታ ያተኮረ መሆኑን አቶ አህመድ ገልጸዋል።

በአገራዊና ቀጣናዊ የሰላም ጉዳዮች ላይ በመነጋገር ሁለቱ አገራት በጸጥታ ጉዳይ በጋራ ለመስራትም ተስማምተዋል።

የጅቡቲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሐመድ አሊ የሱፍ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌ ስኬታማ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

መሪዎቹ በውኃ፣ በሃይል አቅርቦት፣ በመንገድና ወደብ አገልገሎት እንዲሁም አጠቃላይ ከሎጂስቲክስ ዘርፉ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት የውጭ ቋንቋዎችና ዲጂታል ሚዲያ ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም፤ መሪዎቹ በዋናነት ኢትዮጵያና ጅቡቲ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ በሰላምና ደህንነት እንዲሁም በሌሎች በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ቀጣናዊ ትስስር ስለሚጠናከርበት ሁኔታ ላይም በስፋት ተወያይተዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም