ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የሚሳተፉበት ‘ኤችአር 6600’ እና ‘ኤስ 3199’ ረቂቅ ሕጎቹን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በዋሺንግተን ዲሲ ይካሄዳል

መጋቢት 19 ቀን 2014 (ኢዜአ)ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የሚሳተፉበት ‘ኤችአር 6600’ እና ‘ኤስ 3199’ ረቂቅ ሕጎችን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ በዋሺንግተን ዲሲ ይካሄዳል።

ከቀኑ 10 ሰአት ጀምሮ በአሜሪካ መንግስት መቀመጫ ‘ካፒቶል ሂል’ ፊት ለፊት በሚካሄደው ሰልፍ ረቂቅ ሕጎቹ የኢትዮጵያን ሕልውና የሚጎዳ በመሆኑ ውድቅ መሆን አለበት የሚሉ መልዕክቶች በሰልፈኞቹ እንደሚተላለፉ ኢዜአ ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ማህበር የዋሺንግተን ዲሲ ግብረ ሃይል ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ሕጎቹ ለረጅም ጊዜ የቆየውን በኢትዮጵያና አሜሪካ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚጎዱ እንዲሁም የሁለቱን አገራትን ጥቅም የማያስጠብቁ መሆናቸውን የአሜሪካ መንግስት መገንዘብ እንዳለበት የሚያሳስቡ መፈክሮች እንደሚሰሙም ገልጿል።

በሰልፉ ላይ ከአሜሪካ ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በተጨማሪ ኤርትራውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንደሚሳተፉ ተጠቅሷል።

የዛሬው ሰላማዊ ሰልፍ የሚካሄደው ነገ የሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ በ‘ኢትዮጵያ ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ ፕሮሞሽን አክት ኦፍ 2021’ ወይም ‘ኤስ.3199’ ረቂቅ ሕግ ላይ ከሚያደርገው ውይይት አስቀድሞ የሚካሄድ ነው።

ኮሚቴው በረቂቅ ሕጉ ላይ መጋቢት 14 ቀን 2014 ዓ.ም ሊያደርግ የነበረውን ውይይት ማራዘሙ የሚታወስ ነው።

በአሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች በቅርቡ በኒው ጀርዚ ግዛትና በካሊፎርኒያ ግዛት ሳን ፍራንሲስኮ ከተማ ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።

የ‘ኤችአር 6600’ ተጓዳኝ ወይም አጋዥ (ኮምፓኒየን ቢል) የሆነው ‘ኤስ.3199’ በአሜሪካ ሴናተር ሮበርት ሜኔንዴዝ (ኒው ጀርዚ) ዋና አርቃቂነት፣ በሴናተር ጀምስ ሪስች (ኢዳሆ)፣ በሴናተር ክሪስ ኩንስ (ዴልዌር) እና በሴናተር ቶም ቲሊስ (ኖርዝ ካሮላይና) ደጋፊነት የተዘጋጀ ነው።

በአሜሪካ የኮንግረስ አባል ቶም ማሊኖውስኪ (ኒውጀርሲ) ዋና አርቃቂነት፣ በያንግ ኪም (ካሊፎርኒያ)፣ ግሪጎሪ ሚክስ (ኒው ዮርክ)፣ ዴቪድ ሲሲሊን (ሮድ አይላንድስ)፣ ብራድ ሼርማን(ካሊፎርኒያ) እና ማይክል ማካውል (ቴክሳስ) ደጋፊነት የተዘጋጀው ‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ኤችአር 6600 ረቂቅ ሕግ በኮንግረሱ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ውይይት እንደተደረገበት የሚታወስ ነው።

በአሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ረቂቅ ሕጎቹ እንዳይጸድቁ የኮንግረስ አባላትና ሴናተሮችን በማነጋጋርና ማብራሪያ በመስጠት፣ደብዳቤ በመጻፍ፣በማህበራዊ ትስስር ገጾች ዘመቻ በማካሄድና አግባቢ(ሎቢ በመቅጠር) ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም