የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያግዙ ፖሊሲዎችና የፋይናንስ አሰራሮች መሻሻል አለባቸው - ምሁራንና ባለሃብቶች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያግዙ ፖሊሲዎችና የፋይናንስ አሰራሮች መሻሻል አለባቸው - ምሁራንና ባለሃብቶች
አዲስ አበባ ነሀሴ 29/2010 በኢትዮጵያን ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ ኢኮኖሚውን የሚያግዙ ፖሊሲዎችና የፋይናንስ አሰራሮች መሻሻል እንዳለባቸው ምሁራንና ባለሃብቱ ገለጹ። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው መንግስት ለህዝብና ለአገር የሚጠቅሙ የፖሊሲ ሃሳቦች በእቅድና መርሀ ግብሮች በማካተት ለመተግበር ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል። የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር "የኢትዮጵያ የልማት ግቦችና የመዋቅራዊ ሽግግር ፍላጎቶች የአጭርና ረጅም ጊዜ ተግዳሮቶችና እድሎች" በሚል ርዕስ ምሁራንና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ያካተተ ውይይት አድርገዋል። የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን ለማሻሻል፣ የፋይናንስ አሰራር ስርዓቱን ለማዘመን፣ የምርት ጥራትን በማሻሻል የውጭ ንግድን ለማሳደግ አቅም ማሳደግ እንደሚገባ ተገልጿል። የፌርፋክስ አፍሪካ ፈንድ ሊቀመንበርና ኢኮኖሚስት አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር በመፍጠር የፋይናንስ ተቋማትን መዋቅር ማሻሻል ይገባል። የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት በተለይም ባንኮች በቁጥር በርካታ ቢሆኑም የማበደርና የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ለውጥ የመደገፍ አቅማቸው ደካማ መሆኑን ገልጸዋል። ''የትምህርት አሰጣጥ ስርዓቱ ከማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ፍላጎት ጋር የተጣጣመ እንዲሆን የህግ ማዕቀፎች ሊዘጋጁለት ይገባል'' ብለዋል። በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ለማምጣት የአገር ውስጥ ባለሃብቶች በቂ አቅም እንደሌላቸው የጠቆሙት አቶ ዘመዴነህ፤ መንግስት የውጭ ባለሃብቶችን በማበረታታት ከአገር ውስጥ ባለሃብቶች ጋር ማቀናጀት አለበት። ቻይና ኢኮኖሚዋን ማሳደግ የቻለችው የውጭ ባለሃብቶች የአገር ውስጥ ባለሃብቶችን አካተው እንዲሰሩ አስገዳጅ ህግ በማውጣት መሆኑን ገልጸው፤ ''ነገር ግን አስገዳጅ ህጉን ፈርተው እንዳይሸሹ ጥንቃቄ ማድረግም ያስፈልጋል'' ብለዋል። የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ የውጭ ንግድን የሚተኩ ምርቶች ላይ የሚያተኩሩ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችን የሚያበረታታ የህግ ማዕቀፍ ሊኖር እንደሚገባ ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ የሚመረቱ እንደ ቡናና ሰሊጥ አይነት የወጭ ንግድን የሚያሳድጉ ምርቶች እሴት ሳይጨመርባቸው የሚላክበት ሂደት መቆም እንዳለበት ገልጸዋል። በተጨማሪም በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ኢንዱስትሪዎች፣ የግብርና አመራረት ዘዴዎች፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች በቴክኖሎጂ መታገዝ እንደሚገባቸው ተናግረዋል። የበላይነህ ክንዴ አስመጭና ላኪ ባለቤት አቶ በላይነህ ክንዴ የኢትዮጵያን የውጭና ገቢ ንግድ ለማመጣጠን በግብርና ምርትና ምርታማነት ላይ መሰራት እንዳለበት አመልክተዋል። በአገሪቱ በሄክታር እስከ ስምንት ኩንታል ሰሊጥ ማምረት ከሚችሉ ማሳዎች የሚገኘው ምርት ከሁለት ኩንታል እንደማይበልጥ ገልጸዋል። ''መንግስት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ሳይታረሱ የተቀመጡ የእርሻ መሬቶች ወደ ማምረት እንዲገቡ ማድረግ ይገባዋል'' ብለዋል። የኤሌክትሪክ ሃይል፣ መንገድ፣ ውሃና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግብዓቶች ከተሟሉ ምርታማነትን በማሳደግ የንግድ ሚዛኑን ማስተካከል እንደሚቻል ተናግረዋል። በኢትዮጵያ 20 በመቶ ትርፍ በማይገኝበት የንግድ ስርዓት 20 በመቶች የባኮች የብድር ወለድ ለባለሃብቱ ፈተና ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ለውጥ እንቅፋት በመሆኑ ሊፈተሽ እንደሚገባ አመልክተዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው መንግስት ለህዝብና ለአገር የሚጠቅሙ ማንኛውንም የፖሊሲ ሃሳቦችን በእቅድና መርሀ ግብሮች በማካተት ለመተግበር ዝግጁ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ እስከ መጋቢት 2010 ዓ.ም አጠቃላይ ያለባት የውጭ ብድር መጠን 25 ነጥብ 8 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደደረሰ ገልጸዋል። በአገሪቱ ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በከፋ ድህነት ውስጥ መሆናቸውም ጠቁመዋል። በመሆኑም መንግስት ምሁራንና ባለሃብቶች የሚያቀርቧቸውን የፖሊሲ አማራጮች፣ አካሄዶችና የጥናት ውጤቶች ለመተግበር ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል። የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽነር ኢዮብ ተካልኝ መንግስት ካሁን በፊት የነበሩ አሰራሮች ችግር እንዳለባቸው በመገንዘብ የመዋቅር ለወጥ ሊያደርግ መሆኑን ገልጸዋል። መንግስት ውይይት እየተደረገበት ያለውን የትምህርት ፍኖተ ካርታ ጨምሮ ሌሎች ፖሊሲዎችን ለማሻሻል እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመዋል። ምሁራን፣ ባለሃብቶችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ሃሳብ በማመንጨትና አቅጣጫ በማመላከት መንግስትን እንዲደግፉም ጥሪ አስተላልፈዋል።