የኑሮ ውድነትን ለማርገብ የሰላም ማስከበር፣ ግብርናን የማዘመንና የንግድ ስርአቱን የማስተካከል ስራዎች ላይ ማተኮር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የኑሮ ውድነትን ለማርገብ የሰላም ማስከበር፣ ግብርናን የማዘመንና የንግድ ስርአቱን የማስተካከል ስራዎች ላይ ማተኮር ይገባል
ሀዋሳ ፣ መጋቢት 17/2014 (ኢዜአ) መንግስት የኑሮ ውድነትን ለማርገብ የሰላም ማስከበርና ግብርናን የማዘመን እንዲሁም የንግድ ስርአቱን የማስተካከል ስራዎች ላይ ሊያተኩር ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችና ምሁራን አመለከቱ።
የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ማህበር 10ኛው አመታዊ ኮንፈረንሱን ዛሬ በሀዋሳ አካሂዷል።
በማህበሩ የአጋርነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ስሜነህ በሲ እንዳሉት በሀገሪቱ የሚስተዋለው የኑሮ ውድነት ዋነኛ ምክንያቶች የጸጥታ ችግር፣ የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ናቸው።
"በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋለው የጸጥታ ችግር ዜጎች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ እንዳይችሉ ስጋት መፍጠሩና ለግብርና ስራው እንቅፋት በመሆኑ ምክንያት የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ አስተዋጽኦው የጎላ ነው" ብለዋል።
ያለው የሰላም ችግር አርሶ አደሩ ያመረተውን ምርት ወደ ገበያ ለማውጣት እንቅፋት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
"ለኑሮ ውድነቱ የውጪ ሀገራት ጣልቃ ገብነትና የዩክሬንና ራሽያ ግጭት የራሱን አስተዋጽኦ ያበረከተ ቢሆንም በሀገር ውስጥ ያለውን ሰላም ማስከበር ከተቻለ የውጪው ጉዳይ ብዙም ተጽዕኖ አይኖረውም" ብላዋል።
በተጨማሪም የግብርናው ስራ ዘመናዊ አለመሆንና ዛሬም ቀደም እንዳሉት ክፍለዘመናት በበሬ ከማረስ ያልተወጣበት ሁኔታ መኖሩ ችግሩን ያባባሰው መሆኑን አመልክተዋል።
"ሀገራቱ ካላት ዕምቅ ሀብት አንጻር ሲታይ ከፍተኛ አቅም ያለን ቢሆንም አርሶ አደሩ ለግብርና ስራው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲጠቀምና የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ አጠቃቀምን በማሻሻል ምርታማነቱን እንዲያሳድግ ማድረግ ይገባል" ብለዋል ።
"ባጠቃላይ የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ መንግስት ግብርናውን የማዘመንና ሰላም የማስፈን ስራዎችን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል" ሲሉ አስገንዝበዋል።
በኮንፍረንሱ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት ዶክተር አረጋ ሹመቴ በበኩላቸው "መንግስት አቅርቦትን ከፍላጎት ጋር ለማጣጣም ማድረግ ከሚገባው ስራ በተጨማሪ በገበያ ጣልቃ በመግባት ዋጋን ማረጋጋት አለበት" ብለዋል።
"በገበያ ሰንሰለቱ አምራች አርሶ አደሩም ሆነ ሸማቹ ተጠቃሚ አልሆኑም" ያሉት ዶክተርር አረጋ በመካከል ያሉ ደላሎችን በመቆጣጠርና በመከታተል ከግብይት ሰንሰለቱ ውጪ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የምርትና ሸቀጥ የዋጋ ተመን ላይም ተገቢውን ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ በበኩላቸው "በሀገሪቱ ለተስተዋለው የኑሮ ውድነት መባባስ የአቅርቦት እጥረትና ነጋዴው የተጋነነ ዋጋ ጭማሪ ማድረግ እንዲሁም ምርት መደበቅ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው" ብለዋል ።
መንግስት ገበያው በውስን ነጋዴዎች ከመመራት እንዲወጣ ተገቢውን ቁጥጥር ማደረግና በህገወጥ መንገድ የተሰማሩ ነጋዴዎች ላይ ተገቢ የሆነ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ተናግረዋል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት ለማቃለልና በኢኮኖሚው መስክ ሊከተላቸው የሚችሉ አማራጭ ሀሳቦችን በማመንጨት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው አመልክተዋል።
በኮንፍረንሱ ከደቡብና ሲዳማ ክልል የፋይናንስና ኢኮኖሚ ቢሮ ሀላፊዎችና ተወካዮችን ጨምሮ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን ስምንት ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።