መላው ኢትዮጵያዊን "ኤች አር 6600" እንዳይጸድቅ ልንረባረብ ይገባል- የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች - ኢዜአ አማርኛ
መላው ኢትዮጵያዊን "ኤች አር 6600" እንዳይጸድቅ ልንረባረብ ይገባል- የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች
ሀዋሳ፤ መጋቢት 17/2014 ኢዜአ የአሜሪካ መንግሰት በኢትዮጵያ ላይ ለመጣል ያዘጋጀው" ኤች አር 6600ዕ ረቂቅ ህግ በሀገራችን ላይ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን እንዳይጸድቅ ልንረባረብ ይገባል ሲሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ተናገሩ።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎቹ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ረቂቅ ህጉ ሀገሪቱን በኢኮኖሚው ብቻ ሳይሆን በማህበራዊና ፖለቲካው መስክም ከፍተኛ ጉዳት ሊስከትል የሚችል ነው፤
የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ማህበር አባል ዶክተር ስሜነህ በሲ በሰጡት አስተያየት፤ አሜሪካ የራሷን ጥቅም ለማስከበር እንጂ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሰላም በማሰብ የምታደርገው ምንም ነገር እንደሌለ ነው የተናገሩት።
በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ ራሷን ለመቻል የምታደርገው ጥረት ያልተዋጠላቸው ምዕራባውያን በእርዳታ ስም በእጅ አዙር ቅኝ ለመግዛት ያላቸውን ፍላጎት ለማሳካት ሲሉ ማዕቀብ በመጣል ተጽዕኖ ለመፍጠር እየተራወጡ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
መንግስት በትግራይ ክልል ለሚገኙ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቱ የተሳለጠ እንዲሆን ለማድረግ ግጭት የማቆም ውሳኔ መወሰኑ ተገቢና ኤች አር 6600 ረቂቅ ህግ እንዳይጸድቅ ለማድረግ እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል።
ሀገራችን ህግ ለማስከበር ተገዳ የገባችባቸው የህልውና ጦርነት ኢኮኖሚውን በከፍተኛ ደረጃ እንደጎዳው ጠቁመው፤ ይህ ረቂቅ ህግ ቢጸድቅ ከኢኮኖሚው በተጨማሪ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮቻችን ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል።
ረቂቅ ህጉ ለኢትዮጵያ የሚደረግ ብድርና እርዳታ እንዲቆም ከማድረጉ በተጨማሪ በዲፕሎማሲ መስክ ተሰሚነትን የሚያሳጣ፣ በማህበራዊው ዘርፍ ያለው አሉታዊ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ የበደቡብ ክልል ፕላንና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሀላፊና የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ሙባረክ አወሉ በበኩላቸው፤ ይህ ህግ የሀገርን ኢኮኖሚ የሚጎዳ መሆኑን ገልጸዋል።
ረቂቅ ህጉ ከአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በአሜሪካ የሚዘወሩ ምዕራባውያን ሀገራት ማዕቀቡን በመቀበል ብድር እርዳታና ሌሎች ድጋፎችን የሚያሳጣ እንደሆነም አስረድተዋል።
በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖረው መላው ኢትዮጵያዊ፣፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያን የሚወዱ ህዝቦች በሙሉ እንደ በቃ ንቅናቄው በጋራ ሊቃወሙት ይገባል ነው ያሉት።
መንግስት ግጭት የማስቆም ውሳኔ ላይ መድረሱና ተግባራዊ ማድረጉ በአሁኑ ወቅት በአለም አቀፍ ተቋማት ተቀባይነት ያስገኘ መሆኑና የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም የሰጠው አድናቆት ረቂቅ ህጉ እንዳይጸድቅ እንደሚረዳ አቶ ሙባረክ ጠቅሰዋል።
ይህም ሆኖ በሀገሪቱ ላይ ከባድ ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ ባለመዘናጋት ረቂቅ ህጉ እንዳይፀድቅ መላው ኢትዮጵያውያን ከወዲሁ መረባረብ አለብን ነው ያሉት ባለሙያዎቹ።
"ኤች አር 6600” ረቂቅ ሕግ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አጥፊውን ያለየ፣ በአማራና አፋር ክልሎች የደረሰውን ጉዳት የካደና በሉዓላዊ ሀገር ላይ ጣልቃ የሚገባ በመሆኑ ፍጹም ተቀባይነት እንደሌለው የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ቀደም ብሎ አስታውቋል።
ረቂቅ ሕጉ መንግስት ለሰላም እያደረገ ያለውን ጥረት ወደ ጎን የሚተው፣ ኢትዮጵያዊያን ለችግር የሚዳርግ፣ ሀገርን ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የሚያጋልጥ በመሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሰነዱ እንዳይጸድቅ መታገል እንዳለባቸውም እንዲሁ።