ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ አመራሮች ጋር ተባብሮ እንደሚሰራ አስታወቀ

መጋቢት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የደቡብ አፍሪካን አየር መንገድ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን የአየር መንገዱ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ግርማ ዋቄ ገለጹ፡፡

አቶ ተወልደ ገብረማርያም የአፍሪካን ቱሪዝምና የበረራ ኢንዱስትሪ ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ ቁልፍ ሚና እንደተጫወቱ ዓለም አቀፉ የቱሪዝም ኔትወርክ አስታውቋል።

አቶ ግርማ የሰጡትን መግለጫ ተከትሎ የደቡብ አፍሪካው ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን(SABC) እንደዘገበው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አመራር ቡድን ለደቡብ አፍሪካው አየር መንገድ አስፈላጊ በሆነበት ቦታ ሁሉ ድጋፉን ያደርጋል።

የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ ከአፍሪካ ጉልህ አየር መንገዶች አንዱ እንደሆነ የገለጹት የቦርድ ሰብሳቢው “የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ የፖለቲካና ሌሎች ጣልቃ ገብነቶችን በመግታት በአለም አቀፍ ገበያው ተወዳዳሪ እንደሚሆን እናምናለን” ብለዋል።

የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሊፈታ ይችላል ብሎ የሚያምነው ችግር ካለም በትብብር ለመስራት ዝግጅቱ እንዳለ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስራ አመራር ቦርድ በጤና ችግር ምክንያት ስራቸውን በለቀቁት የቀድሞው ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ምትክ አቶ መስፍን ጣሰውን መመደቡ ይታወሳል።

በተያያዘ ዜና አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም የአፍሪካን ቱሪዝምና የበረራ ኢንዱስትሪ ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው ዓለም አቀፉ የቱሪዝም ኔትወርክ አስታውቋል።

የኔትወርኩ ምክትል ፕሬዝዳንት አላይን አንጌ( Alain St.Ange) የአፍሪካ የበረራ ኢንዱስትሪ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲራመድ አቶ ተወልደ ከፍተኛው ሚና ተጫውተዋል።

ባጋጠማቸው የጤና ችግር ምክንያት ከእድሜያቸው ቀድመው ጡረታ ቢወጡም በአፍሪካ የበረራ ኢንዱስትሪ ላይ አዲስ ከፍታ ማስመዝገብ መቻላቸውን ገልጸዋል።

ሁሉም የአፍሪካ ሃገራት የቱሪዝም ሚኒስትሮች በአቶ ተወልደ ገብረማርያም ተግባር አድናቆትና ክብር ይሰማቸዋል፤ እሳቸው የበረራ ኢንዱስትሪ ከፍ ብሎ የማየት ህልም ያላቸው ናቸው” ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ  አቶ ተወልደ እስከ ዛሬ ላደረጉት አስተዋጽኦም አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም