ቀጥታ፡

ኤችአር 6600 ረቂቅ ሕግ እንዳይጸድቅ ሁሉም ጥረት እንዲያደርግ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጥሪ አቀረበ

መጋቢት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኤችአር 6600 ረቂቅ ሕግ እንዳይጸድቅና የሀገር ውስጥ ችግሮች ከምንጫቸው እንዲደርቁ ሁሉም የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጥሪ አቀረበ።

ረቂቅ ሕግ እንዳይጸድቅና የሀገር ውስጥ ችግሮችን ለመፍታት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሁሉም አካል የበኩሉን መወጣት እንዳለበትም ጉባኤው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሰሜን አሜሪካ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤውን የጉባኤው ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፣ አምባሳደር ፍጹም አረጋና የሠባቱ የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት በሲልቨር ስፕሪንግ ሜሪላንድ አካሂዷል።

በጉባኤው በአሁኑ ወቅት በሚታዩ የውስጥና የውጭ ተግዳሮቶችና መፍትሔውን በተመለከተ ምክክር መካሄዱን የጉባኤው ጠቅላይ ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ባደረግነው የመጀመሪያ የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባም የሚከተሉትን የአቋም መግለጫዎች አውጥተናል ብለዋል።

በሰሜን አሜሪካ ውስጥ የሚገኙትን የኢትዮጵያ ሃይማኖቶች በማስተባበር ለጋራ ቤታችን ኢትዮጵያ በሰላም፣ በፍትሕና በልማት አቅጣጫ በጎ አስተዋጽኦ ለማድረግ ያመቸን ዘንድ በሂደት በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ የጉባኤውን ምዕራፍ (ቻፕተር) ለማቋቋም ተስማምተናል ነው ያሉት።

በአሜሪካ ኮንግረስ ሊቀርብ ያለው ኤችአር 6600 እና በሴኔት ሊቀርብ በዝግጅት ላይ ያለው ኤስ 3199 የኢትዮጵያን ሕዝብ ኢኮኖሚ የሚጎዳና የኩሩውን ሕዝብ ሉዓላዊነት የሚዳፈር ሆኖ ስላገኘነው እንዲቆም ወይም እንዲለወጥ ለሚመለከተው አካል በደብዳቤ ጥያቄ ለማቅረብ የተስማማን ሲሆን ምዕመናኖቻችን ይህን ተረድተው ተቃውሟቸውን እንዲያሰሙ ለመጠየቅ ተስማምተናል ሲሉ ገልጸዋል።

በአገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ሥፍራዎች ያሉ ግጭቶች እንዲቆሙ፣ በሰሜን፣ በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እንዲሁም በሌሎችም ተመሳሳይ ችግሮች ባሉባቸው አካባቢዎች ያለው ሰብዓዊ ቀውስ እንዲፈታ የሚመለከታቸው ወገኖች ሁሉ የተቻላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ፣ ችግሮች ከመከሰታቸው አስቀድሞ ከምንጫቸው እንዲደርቁ መንግሥትም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የበኩላቸውን ጥረት እንዲወጡ እንጠይቃለን በማለትም አሳስበዋል።

በአገራችን በተለያዩ ሥፍራዎች የሚፈጸሙ ግድያዎች፣ ማፈናቀሎች፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የፍትህ መጓደሎች እንዲቆሙ፣ እንዲወገዙ እና አጥፊዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ሁሉንም አካል እንጠይቃለን ነው ያሉት።

በሰሜን አሜሪካ በየቤተእምነቱ የሚገኙ ምዕመናን ባለው ሁኔታ ሳይለያዩ፣ ይልቁንም የገጠመንን አገራዊ ችግር በትብብር መፍታት ይቻል ዘንድ አንድነታቸውን ጠብቀው አምልኳቸውን እንዲፈጽሙ ጠቅላላ ጉባኤው ማመልከቱን ተናግረዋል።

ምንም እንኳ ሰው በገዛ አገሩ ከመኖሪያ ቀዬው መፈናቀሉ የማይገባና አሳዛኝ ክስተት ቢሆንም አስገዳጅ ሁኔታዎች በሚከሰቱበት ወቅት እያንዳንዱ ማህበረሰብ ለተፈናቃዮች የሚያሳየውን በጎ አቀባበል እያደነቅን ይህ ዓይነቱ የመደጋገፍ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንጠይቃለን በማለት ጉባኤው መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም