የህዳሴ ግድብ ግንባታ ገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞች ከፍተኛ ውጤት አስገኝተዋል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ ግንባታ ገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞች ከፍተኛ ውጤት አስገኝተዋል ተባለ
አዲስ አበባ ግንቦት 10/2010 ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ገቢ ለማሰባሰብ የተካሄዱ ሁነቶችና ፕሮግራሞች ከሚጠበቀው በላይ ውጤት ማስገኘታቸው ተገለጸ። ዝግጅቶቹ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎባቸው በመተግበራቸው አፈጻጸማቸው ከእቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን የግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ገልጿል። ፅህፈት ቤቱ በሰጠው ዛሬ መግለጫ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከተካሄዱ ሁነቶችና ፕሮግራሞች 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል። የጽህፈት ቤቱ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም እንዳሉት የታቀዱ ሁነቶችና ፕሮግራሞች ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎባቸውና የጋራ መግባባት ተፈጥሮ ወደ ስራ በመገባቱ ህዝባዊ ተሳትፎው አድጓል። በዚህም እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ለመሰብሰብ ታቅዶ በዘጠኝ ወር 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መሰብሰብንና ይህም ከዕቅድ በላይ ማከናወን ተችሏል። አቶ ኃይሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ችቦ፣ የሰላም ዋንጫ፣ የብሄር ብሄረሰቦች ዋንጫ ንቅናቄን በመፍጠር ድጋፍ ማሰባሰብ መቻሉን ገልፀዋል። የግድቡ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን 7ኛ ዓመት አስመልክቶ በተዘጋጁ የንባብ ሳምንት፣ የአባይ ዘመን ስነ-ጥበብ ምሽት፣ እግር ኳስ ውድድር፣ የባለሃብቱ የግድቡ ጉብኝት፣ የቦንድ ሽያጭ ሳምንትና መሰል ዝግጅቶች ድጋፉ መገኘቱን ነው ያብራሩት። በተፈጠረው ንቅናቄ ከገንዘብ ድጋፉ በተጨማሪ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ መከናወኑንም ተናግረዋል። የባለሃብቱን ተሳትፎ ለማሳደግም ግድቡን እንዲጎበኙ መደረጉን ገልፀው ድጋፉ ቀጣይነት እንዲኖረው በቀጣይ ውይይት ለማካሄድ መታቀዱንም ነው ያስረዱት። የዲያስፖራውን ድጋፍ ለማጠናከርም በተለያዩ ቋንቋዎች ጽሁፎች ተዘጋጅተው እንደተሰራጩ ገልፀዋል። እስካሁን ለግድቡ ግንባታ ከኅብረተሰቡ በተለያየ መንገድ ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉ ተገልጿል።