የመንግስት የግጭት ማቆም ውሳኔ በዲፕሎማሲው መስክ ትልቅ ድል አስገኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስት የግጭት ማቆም ውሳኔ በዲፕሎማሲው መስክ ትልቅ ድል አስገኝቷል
መጋቢት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) “የመንግስት የግጭት ማቆም ውሳኔ በዲፕሎማሲው መስክ ትልቅ ድል አስገኝቷል” ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
በአማራ ክልል 11 ሚሊዮን፣ በአፋር ክልል 1 ነጥብ 3፣ በሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች ድርቅ ከ3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ስለሚያስፈልግ አገራዊና ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ሰብዐዊ ድጋፍ አቅርቦት ላይ እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርቧል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በወቅታዊ ጉዳዮች በሰጡት መግለጫ ከቀናት በፊት የሰብዓዊ እርዳታ ለማፋጠን የግጭት ማቆም የመንግስት ውሳኔን አንስተው፣ ውሳኔው ለተጎጂዎች ድጋፍ አሰጣጡን ለማፋጠን የተወሰደ እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል።
የትግራይ ተወላጆች ጉዳት ወደ ደረሰበት ወደ አማራ አዋሳኝ እየመጡ በመሆኑና ይህም በክልሉ ላይ የሚፈጠረውን ውስብስብ ችግር ለመቅረፍ ተፈናቃዮች ባሉበት ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ነው ብለዋል።
የግጭት ማቆም እርምጃው ገቢራዊ እንዲሆን መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው፤ የውሳኔ ሀሳቡ ስኬታማነት ግን የሌላውን ወገን ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ጉዳይ በመሆኑ ሌላኛውም አካል ተባባሪ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።
ውሳኔውን ተከትሎ አንገብጋቢ ድጋፍ የሚጠይቁ ዜጎች ከመንግሥት ተጨማሪ ዓለም አቀፍ የረድኤት ተቋማትም እጃቸውን ሊዘረጉ እንደሚገባ ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ የገለጹት።
ውሳኔው የዜጎችን ሰብአዊነት ያስቀደመ ነው በሚል የተለያዩ አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት እንደደገፉት ገልጸው፤ ውሳኔው በዲፕሎማሲው መስክ ትልቅ ድል ያመጣ ነው ብለዋል።
ውሳኔውን ከመደገፍ ባለፈ ድጋፉ ተግባራዊ እርምጃ ስለሚጠይቅ አገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሰብዓዊ እርዳታ እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርበዋል።
በአማራ ክልል ዋግኸምራ አካባቢ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የዕለት ደራሽ ምግብ እንደሚሹ ገልጸው፤ በቆቦ አካባቢ በርካታ ተፈናቃዮች በመኖራቸው አዲስ ጊዜያዊ መቆያ ጣቢያ ተቋቁሞ የመጠለያ፣ የምግብ፣ የጤና እና ሌሎች ቁሳቁሶች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በጦርነቱ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ተፈናቃዮች በአማራ ክልል እንዳሉና ከነዚህም ውስጥ እስካሁን 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች ወደ መኖሪያቸው ተመልሰዋል ብለዋል።
ነገር ግን እነዚህን ጨምሮ በክልሉ 11 ሚሊየን ዜጎች ለምግብ ዋስትና ችግር በመጋለጣቸው ድጋፉ መጠናከር እንዳለበት አመልክተዋል።
በአፋር ክልል 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች መፈናቀል ደርሶባቸው እንደነበር ገልጸው፤ በተለይም በድጋሚ ወረራ ምክንያት ለተፈናቀሉ 70 ሺህ ገደማ ዜጎች የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽ መደረጉን ተናግረዋል።
በሶማሌ ክልል እና ኦሮሚያ ክልሎች በተከሰተው ድርቅ አንገብጋቢ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ተደራሽ እየሆነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ቅርቡ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የዜጎች የውይይት መድረኮች መካሄዳቸውን አውስተው፤ በተለይም በ21 መድረኮች የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚዎች ማወያየታቸውን አንስተዋል።
መንግስት የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ስራውን ጀምሯል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በቀጣይም መደማመጥን መሰረት ያደረጉ የፖለቲካ ስርዓት ለመገንባት የሚደረጉ ውይይቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
ከ‘ኤች አር 6600” ረቂቅ ሕግ በተያያዘ በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት እና በርካታ ጎጂ ጉዳዮች የተካተተበት እንደሆነ ተናግረዋል።
ረቂቅ ሕጉ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አጥፊውን ያለየ፣ በአማራና አፋር ክልሎች የደረሰውን ጉዳት የካደና በሉዓላዊ አገር ላይ ጣልቃ የሚገባ በመሆኑ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።
ረቂቅ ሕጉ መንግስት ለሰላም እያደረገ ያለውን ጥረት ወደ ጎን የሚተውና ኢትዮጵያዊያን ችግር የሚዳርግና አገርን ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የሚያጋልጥ በመሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሰነዱ እንዳይጸድቅ መታገል አለባቸው ነው ያሉት።
መንግስት ሰነዱ እንዳይጸድቅ የዲፕሎማሲ ስራዎችን እየሰራ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት ድጋፍ እንደሚያሻት ገልጸው፤ ረቂቅ ሕጉ ተጨማሪ ጫና የሚፈጥር በመሆኑ ውጫዊ ጫናዎችን መቋቋም የሁሉም ኃላፊነት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ