ቀጥታ፡

ከእንሰት የሚገኘውን ጥቅም ዘላቂነት ለማረጋገጥ ስነ ምህዳሩን መጠበቅ የሚያስችል የፖሊስ ማዕቀፍ ሊኖር እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ ነሀሴ 29/2010 ከእንሰት የሚገኘውን ጥቅም ዘላቂነት ለማረጋገጥ ስነ ምህዳሩን መጠበቅ የሚያስችል የፖሊስ ማዕቀፍ ሊኖር እንደሚገባ ተገለጸ፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የፌደራል ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት በዘርፉ በተካሄዱ ጥናቶች ዙሪያ በሃዋሳ የምክክር መድረክ ተካሄዷል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርና የጉለሌ እጽዋት ማእከል ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው በመድረኩ ላይ እንደገለፁት ከሁለት ዓመት በፊት በዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን በጥናት መለየት የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆኗል፡፡ ኘሮጀክቱ በሃገር ውስጥ ያሉ ሶስት ዩኒቨርሲቲዎችና የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ከእንግሊዙ ሌስተር ዩኒቨርሲቲና ሮያል ቦስተን ጋርደን ጋር በትብብር ነው የተካሄደው፡፡ ፕሮፌሰር ሰብስቤ እንዳሉት ጥናቱ የተካሄደው እንሰት ተጠቃሚ በሆኑት ደቡብ፣ በከፊል ኦሮሚያና ጋምቤላ ክልሎች ሲሆን በዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶች የመለየት ስራ ተሰርቷል፡፡ የጥናቱ ውጤት እንደሚያሳየውም ከ40 ዓመታት በላይ የተሰሩ የተለያዩ ጥናቶች ቢኖሩም የተበጣጠሱና ተሰንደው ያልተቀመጡ በመሆናቸው ተገቢውን መረጃ የያዙ አይደሉም፡፡ በየአካባቢው ያሉ ከ150 በላይ የእንሰት ዝርያዎችም በሳይንስ ያልተደገፉ በመሆናቸው ምርታማነቱን ማሳደግ አልተቻለም፡፡ በመሆኑም ከእንሰት የሚገኘውን ጥቅም ዘላቂነት ለማረጋገጥ ስነ ምህዳሩን መጠበቅ የሚያስችል የፖሊስ ማእቀፍ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም የሚያደርጓቸውን ምርምሮች በተገቢው ማሳየት የሚያስችል የልህቀት ማእከል በሃገር ደረጃ ሊኖር እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ አሁን ባለው አሰራር የእንሰት ሰብልን ማቆየት አይቻልም ያሉት ፕሮፌሰሩ እንደሌሎች ሰብሎች በኤክስቴሽን ፓኬጅ ማገዝ እንደሚያስፈልግና ተመራማሪዎች የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠቁመዋል፡፡ በመድረኩ ላይ ጥናታዊ ጽሀፍ ያቀረቡት የኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማሪዮ በበኩላቸው በደቡብና ደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ከ2 ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎች እንሰት ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ ''በተለያዩ በሽታዎች መጠቃት፣ የእንሰት ሰብልን በሌላ መተካት፣ የግብይት ስርዓቱ ደካማ መሆንና በግብርናው መስክ ለእንሰት የሚሆን የፓኬጅ አጠቃቀም አለመዘርጋቱ የተረሳ ሰብል አድርጎታል'' ብለዋል፡፡ በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት የእንሰት ተክል ዘላቂነት ያለው ጥቅም እንዲሰጥ በጥናት መደገፍ እንደሚያስፈልግና የጥናት ውጤቱን ለፖሊስ አውጭዎች ግብዓት ሊሆን በሚችል መልኩ መዘጋጀት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ የብዝሃ ህይወት ኢንስቲቲዩት ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ የዳሰሳ ጥናት ማድረጉን የገለጹት ዶክተር መለሰ በደቡብ ክልል ከምባታ ጠምባሮ ዞን አንጋጫ ወረዳ 88 የተለያዩ ዓይነት ዝርያዎችን የመጠበቅና የማባዛት ስራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በጂማም ተመሳሳይ ስራ እየተከናወነ ሲሆን ከምግብነት ባለፈ አብዛኛው ህዝብ ለመድሃኒትነት የመጠቀም ልምዱን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ በመደግፍ አርሶአደሩን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡ የሰብሉን ስነ ህይወታዊ አረባብ ዘዴ በዘረ መል ደረጃ በማጥናት በተለይም በሽታን መቋቋም የሚችሉ ዝርያዎችን መለየትና ምርቱ በአጭር ጊዜ እንዲደርስ ለማድረግ የተጀመሩ የምርምር ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ በደቡብ ክልል ከሩብ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በእንሰት እየለማ መሆኑን የገለፁት ደግሞ  የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ ናቸው፡፡ ምርታማነቱም በሄክታር እስከ 310 ኩንታል መሆኑን ገልፀዋል፡፡ እስከ አምስት አመት ቆይቶ ለምርት የሚደርሰው የእንሰት ሰብል አነስተኛ ምርት ከመስጠቱና ከተለያዩ ችግሮች አንጻር በርካታ አርሶአደሮች በሌላ ሰብል እንደሚቀይሩት ተናግረዋል፡፡ የምርታማነት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂ እጥረት፣ የተሸሻሉ ዝርያዎች አቅርቦት ውስንነት፣ የቅድመና ድህረ ምርት አያያዝ፣ የእሴት ሰንሰለትና የግብይት ስርዓቱ ደካማ መሆን በዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እያለው ትኩረት ያላገኘው እንሰት እንደ ሃገር የራሱ የሆነ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና አቅጣጫ የሚሻ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት ለጀመሩት ስራ ውጤታማነት የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡ ትናንትና ዛሬ በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ በዘርፉ ምርምር ያደረጉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራማሪዎች የተገኙ ሲሆን በቀረቡ ጥናታዊ ጽሁፎችና በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ መክረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም