ቀጥታ፡

ጀርመን በኢትዮጵያ የሚካሄደው ብሔራዊ ምክክር እንዲሳካ የበኩሏን ድጋፍ ታደርጋለች

መጋቢት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) ጀርመን በኢትዮጵያ የሚካሄደው ብሔራዊ ምክክር እንዲሳካ የበኩሏን ድጋፍ እንደምታደርግ በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፋን አወር ገለጹ።

አምባሳደር ስቴፋን አወር ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ሰላም መሆን ለአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ብሎም ለአህጉሪቷ መረጋጋት ሚናው የጎላ ነው፡፡

በዚህም ጀርመን በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገትና የፖለቲካ መረጋጋት እንዲሰፍን ጽኑ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።

እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2019 ጀርመንና ኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች በትብብር ለመስራት ስምምነት መፈራረማቸውንም አስታውሰዋል፡፡

ጀርመን በተለይ በኢኮኖሚና የዴሞክራሲ ለውጦች ላይ በጋራ ለመስራት የተደረሱ ስምምነቶችን ውጤታማ እንዲሆኑ እንደምትሰራም ነው የተናገሩት፡፡

ጀርመን በኢትዮጵያ የተረጋጋ የዴሞክራሲና ፖለቲካዊ ምህዳር እንዲኖር ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷን ያነሱት አምባሳደሩ፤ አገራቸው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ለሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ድጋፍ ማድረጓን ለአብነት አንስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሊካሄድ የታቀደው ብሔራዊ ምክክር እንዲሳካም የበኩሏን ድጋፍ እንደምታደርግም ተናግረዋል፡፡

ምክክሩ በአገሪቷ ውስጥ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ሚናው የጎላ መሆኑንም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሚገጥሟትን ችግሮች እንድትሻገር ጀርመን ሁሌም ከጎኗ ትቆማለች ሲሉም ነው አምባሳደር ስቴፋን አወር የተናገሩት፡፡

ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በግብርናና ሌሎች መስኮች ያላትን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር እንደምትሻም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያና የጀርመን የሁለትዮሸ ግንኙነት የጀመሩት እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1905 እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያመላክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም