ቀጥታ፡

በባቢሌ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ዝሆኖችን ከጥፋት ለመታደግ ባለድርሻ አካላት በትብብር መስራት እንዳለባቸው ተመለከተ

ሐረር ፤ መጋቢት 17/2014 (ኢዜአ) በባቢሌ መጠለያ ጣቢያ እየተመናመኑ የመጡትን ዝሆኖች ከጥፋት ለመታደግ ባለድርሻ አካላት በትብብር መስራት እንዳለባቸው ተመለከተ።

በኦሮሚያና ሱማሌ ክልሎች የሚያዋስነው የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ከተጋረጠበት አደጋ ማዳን በሚቻልበት ዙሪያ  የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የምክክር መድረክ በሐረር ከተማ  እየተካሄደ ነው።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ባለስልጣን ጋር በመተባበር ባዘጋጀው በዚህ መድረክ ላይ  የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አደም መሃመድ እንደገለጹት፤ በመጠለያው ባለፉት ስምንት ወራት 11 ዝሆኖች ተገድለዋል።

ለዚህም ምክንያቱ ከህገወጥ ሰፈራ፣ ደን ጭፍጨፋና  የእርሻ መስፋፋት ጋር ተያይዞ  መሆኑን አስረድተዋል።

ያልተጠኑ ኢንቨስትመንት ፍቃዶች ሙስናና ብልሹ አሰራሮችም ሌላ ለችግሩ መንስዔ  መሆናቸውን አመላከተዋል።

በ1963 ዓም የተቋቋመው የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ በውስጡ  600 የዝሆኖች ቁጥር እንደነበረው አስታውሰው፤   አሁን ላይ 300 መድረሱን አስታውቀዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ  የምርምር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ተስፋዬ ለማ በበኩላቸው፤ በባቢሌ መጠለያ የሚገኙ  ዝሆኖች ለመታደግ በጥናትና ምርምር  ከማገዝ ባለፈ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ ጣቢያን ከሚደርስበት ሰው ሰራሽ አደጋ ለመታደግ እና ህልውናውን ለማረጋገጥ  በአለም አቀፍና በሀገር ውስጥ የዱር እንስሳት መርሆዎች መስተዳደር እንደሚገባው የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ባለስልጣን ምክትል ዋና ባለስልጣን አቶ ሰለሞን መኮንን ናቸው።

በመጠለያ ጣቢያው የተጋረጠውን አደጋ ለመቀነስ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ከማስጨበጥ ሌላ  ለመጠለያው አጎራባች ከሆኑ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች  ጋር በትብብር መስራት እንደሚገባ  አመልክተዋል።

በኦሮሚያ እና ሱማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚገኘው  የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ  በ6ሺ 983 ስኩየር ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን ፤  "ሎኮ ሳንዳታ አፍሪካ "የተባለውን የዝሆን ዝርያ ፣ባለ ጥቁር ጋማ አንበሳና የበርካታ አዕዋፍ መገኛም መሆኑን በመድረኩ ላይ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም