“ኤች አር 6600 ረቂቅ ሕግ ኢትዮጵያውያንና ምስራቅ አፍሪካውያንን ለመከፋፈልና ለማዳከም የተዘጋጀ ነው” ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ - ኢዜአ አማርኛ
“ኤች አር 6600 ረቂቅ ሕግ ኢትዮጵያውያንና ምስራቅ አፍሪካውያንን ለመከፋፈልና ለማዳከም የተዘጋጀ ነው” ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ
መጋቢት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ)“ኤችአር 6600 ረቂቅ ሕግ ኢትዮጵያውያንና ምስራቅ አፍሪካውያንን ለመከፋፈልና ለማዳከም የተዘጋጀ ነው”ስትል ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ ገለጸች።
ዳያስፖራው ኢትዮጵያውያን ለመከፋፈል የተዘጋጀውን ሕግ በአንድነት በመቆም እንዲታገል ጥሪ አቅርባለች።
ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግ አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጿ ባስተላለፈችው መልዕክት ሕጉ ‘በኢትዮጵያ ሰላም፣መረጋጋትና ዴሞክራሲ አመጣለሁ” ቢልም በተቃራኒው ኢትዮጵያን የሚጎዳ መሆኑን ገልጻለች።
“ኤችአር 6600” ረቂቅ ሕግ ኢትዮጵያውያንና ምስራቅ አፍሪካውያንን ለመከፋፈልና ለማዳከም የተዘጋጀ ነው ብላለች።
የሕጉ አርቃቂዎች “ስለ ኢትዮጵያውያን፣ኤርትራውያንና ምስራቅ አፍሪካውያን ግድ አይሰጣቸውም፤ አሁንም በኢትዮጵያ ጦርነቱን የጀመረው ሕወሓት መሆኑን ሁልጊዜ እንዳላየ እያለፉት ነው” ስትል ገልጻለች።
የሕወሓት እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ያለው ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት እየተደረገ ያለውን ስራ ይበልጥ አስቸጋሪ እንዳደረገው አመልክታለች።
የረቂቅ ሕጉ አርቃቂዎች የሕወሓት ደጋፊዎችና ቡድኑ የፈጸማቸውን ወንጀሎች መሸፈን የሚፈልጉ መሆናቸውንና ሕጉ የተጻፈውም የሕወሓት ደጋፊዎች ለተወሰኑ የኮንግረስ አባላት በከፈሉት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መሆኑን ተናግራለች።
“ኤችአር 6600” ሕወሓት ላይ ምንም አይነት እርምጃ እንዲወሰድ የሚያደርግ አንቀጽ የለም ብላለች።
“በሕጉ አማካኝነት የአሜሪካ መንግስት በትግራይ የዘር ማጥፋት ተፈጽሟል የሚለውን ይወስናል የሚለው ለወታደራዊ ጣልቃ ገብነት የሚጋብዝ አደገኛ ሀሳብ ነው” ስትል ነው ጋዜጠኛ ሄርሜላ የገለጸችው።
ረቂቅ ሕጉ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ያሻሽለዋል የሚሉ አንዳንድ ወገኖች አሉ፤በተቃራኒው ሕጉ በኢትዮጵያ ያለውን ችግር የሚያባብስ እንደሆነ አመልክታለች።
በማዕቀብ ለውጥ እንደማይመጣና ችግር አባባሽ መሆኑን ከኢራቅ፣ሊቢያ፣አፍጋኒስታንና ሶሪያ የተሻለ የታሪክ ማሳያ ሊኖር እንደማይችል ገልጻለች።
ረቂቅ ሕጉ በአሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት ለኢትዮጵያ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ የማስቆም አላማ ያለው ነው ብላለች።
ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለመከፋፈል የተዘጋጀውን ኤች አር 6600 እንዳይጸድቅ ዳያስፖራው በአንድነት በመቆም እንቅስቃሴ ሊያደርግ እንደሚገባ ገልጻለች።
እውነት ያሸነፋል ኢትዮጵያም ሰላም የምትሆንበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ተናግራለች።
ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ ከነገ በስቲያ ‘ኤችአር 6600’ እና ‘ኤስ 3199’ ረቂቅ ሕጎች በመቃወም በዋሺንግተን ዲሲ የአሜሪካ መንግስት መቀመጫ ‘ካፒቶል ሂል’ ፊት ለፊት በሚካሄደው ሰልፍ ላይ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በመሳተፍ ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ጥሪ አቅርባለች።
የ’ኤች አር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ሰልፍ ትናንት በካሊፎርኒያ ግዛት ሳን ፍራንሲስኮ ከተማ መካሄዱ የሚታወስ ነው።
በአሜሪካ የኮንግረስ አባል ቶም ማሊኖውስኪ (ኒውጀርሲ) ዋና አርቃቂነት፣ በያንግ ኪም (ካሊፎርኒያ)፣ ግሪጎሪ ሚክስ (ኒው ዮርክ)፣ ዴቪድ ሲሲሊን (ሮድ አይላንድስ)፣ ብራድ ሼርማን(ካሊፎርኒያ) እና ማይክል ማካውል (ቴክሳስ) ደጋፊነት የተዘጋጀው ‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ኤችአር 6600 ረቂቅ ሕግ በኮንግረሱ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ውይይት እንደተደረገበት የሚታወስ ነው።
ዳያስፖራው ሕጉ እንዳይጸድቅ የኮንግረስ አባላት በማነጋገር፤ደብዳቤ በመጻፍና አግባቢ(ሎቢስት) በመቅጠር ጥረት እያደረጉ ይገኛል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ