የግንባታ ፕሮጀክቶችን ሂደት በቅርበት የመከታተል ውስንነት ለግንባታ ሥራዎች ጥራት መጓደል ዋነኛው መንስኤ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የግንባታ ፕሮጀክቶችን ሂደት በቅርበት የመከታተል ውስንነት ለግንባታ ሥራዎች ጥራት መጓደል ዋነኛው መንስኤ ነው
መጋቢት 16/2014/ኢዜአ/ የግንባታ ፕሮጀክቶችን ሂደት በቅርበት የመከታተል ውስንነት ለግንባታ ሥራዎች ጥራት መጓደል ዋነኛው መንስኤ መሆኑን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ገለጸ።
ባለሥልጣኑ በደሴ ከተማ ዘርፉን ማጠናከር በሚቻልበት ጉዳዮች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ነገዎ፤ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ከፍተኛ ገንዘብ የሚዘዋወርበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለሌብነት የተጋለጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ዘርፉን በአግባቡ መምራት ይገባል ነው ያሉት፡፡
የበለጸጉ አገራት ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠርና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሌብነትን ከመቀነሳቸው ባሻገር የዘርፉን አፈጻጸም ጥራትና ፍጥነት ማሻሻል ችለዋል ብለዋል።
የግንባታ ፕሮጀክቶችን ዲዛይን የመገምገምና የመቆጣጠር ውስንነት ለግንባታ ሥራዎች ጥራት መጓደል ዋነኛው መንስኤ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተቋማዊ አደረጃጀት በመፍጠር ችግሩን ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በግንባታ ሂደት ላይ የሚደረግ ጥብቅ ክትትል ለፕሮጀክቶች ጥራትና ፍጥነት ሚናው የጎላ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በባለቤትነት የሚመሯቸው ታላላቅ አገራዊ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ፍጥነትና ጥራት መጠናቀቃቸውን ለማሳያነት ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የግንባታ ሥራዎችን የሚቆጣጠር ተቋም እንዳልነበር አስታውሰው፤ ይህም በዘርፉ ላይ ሥር የሰደደ ብልሹ አሰራር እንዲስፋፋ አድርጎ መቆየቱን ገልጸዋል።
ከለውጡ በኋላ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ ስለመሆኑም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ማተቤ አዲስ፤ ባለሥልጣኑ ባለፉት ሦስት ዓመታት 381 የግንባታ ፕሮጀክቶችን ዲዛይን ገምግሟል ብለዋል።
በዚህም የፕሮጀክቶችን ዲዛይን የመገምገምና የመቆጣጠር ውስንነት እንዲሁም ተቋራጭና አማካሪ መምረጥ ሂደት ላይ የነበሩ ችግሮች ለግንባታ አፈጻጸም ጥራት መጓደል ዋነኞቹ ምክንያቶች መሆናቸው ተለይተዋል ነው ያሉት፡፡
ባለሥልጣኑ በዩኒቨርሲቲዎች ሲከናወኑ የነበሩና ተቋርጠው የቆዩ 758 የግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር ቁጥጥር ማድረጉን ገልጸው፤ በዚህም በግንባታ ሂደት ላይ የነበሩ አምስት የመምህራን ኮንዶሚኒየም ቤቶች በጥራት መጓደል ምክንያት እንዲፈርሱ መደረጉን አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን በግንባታ ዘርፍ ደረጃ የማውጣት፣ ቁጥጥር የማድረግ፣ ፈቃድ የመስጠትና አቅም የመገንባት ኃላፊነት በአዋጅ ቁጥር 1263/2014 ተሰጥቶታል።