ተቋማት በህልውና ዘመቻው ያሳዩትን ትብብርና ቅንጅት የኢንቨስትመንት ዘርፉንለማጎልበት መድገም ይጠበቅባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
ተቋማት በህልውና ዘመቻው ያሳዩትን ትብብርና ቅንጅት የኢንቨስትመንት ዘርፉንለማጎልበት መድገም ይጠበቅባቸዋል
መጋቢት 16/2014/ኢዜአ/ ተቋማት በህልውና ዘመቻው ያሳዩትን ትብብርና ቅንጅት የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማጎልበት መድገም እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዘጋጅነት አገራዊ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የቅንጅት መድረክ ውይይት የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በታደሙበት ዛሬ ተካሂዷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ ዓለም አቀፋዊና የአገር ውስጥ ነባራዊ ሁኔታን ታሳቢ በማድረግ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማምጣት መሥራት ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት ጋር ያላትን የንግድ ሚዛን ለማመጣጠን ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ማብዛት፣ ገቢ ምርቶችን መተካትና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ትኩረት መደረጉንም ገልጸዋል።
በዘርፉ ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል እንዲሁም ማበረታቻዎችን በመተግበር የኢንቨስትመንት መስኩን ማስፋፋት እንደሚገባም እንዲሁ።
የፌዴራልና የክልል ተቋማት በህልውና ዘመቻው ወቅት ከነበራቸው ትብብርና ቅንጅት ልምድ በመውሰድ የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለማጎልበት መሥራት እንዳለባቸውም አመላክተዋል።
ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያን በተለያዩ የዓለም አገራት የሚወክሏት ሚሲዮኖች ከፖለቲካ ዲፕሎማሲ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲ ላይ በትኩረት እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ በበኩላቸው፤ የፀጥታ መስተጓጎልና ህገ-ወጥነት የኢንቨስትመንት ዘርፍን በማጎልበት ረገድ ችግር እየፈጠረ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በተጨማሪ የአስፈጻሚ አካላት አቅም ማነስ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የመሬት አቅርቦት እንዲሁም የመሰረተ ልማት ችግሮች የዘርፉ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ይህም በአገሪቱ ኢንቨስትመንት ፍሰትና የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ አሉታዊ ጫና በማሳደሩ ዘርፉን እየፈተነ እንደሆነ አብራርተዋል።
ለባለሀብቶች የሚተላለፉ ቦታዎች መሰረተ ልማት ያልተሟላላቸው እና ጥናት ያልተደረገባቸው መሆንም የውጭ ባለሃብቶች ወደ ሥራ ለመግባት ከሦስት ዓመት በላይ እንዲጠብቁ ማድረጉን ተናግረዋል።
በተለይም አማራ፣ ኦሮሚያ፣ አዲስ አበባና ጋምቤላ ክልሎች በዚህ ረገድ ቅሬታዎች እንደሚነሱባቸው ገልጸው፤ በተጠቀሱት ክልሎች ቅሬታዎቹን ለመፍታት መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብ የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡንም ኮሚሽነሯ ጨምረው ገልጸዋል።
በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባ በመጠቆም፡፡
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከልም የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ በበኩላቸው፤ ዘርፉን ለማሳደግ ባለሃብቶች የሚያነሱትን ችግር መፍታት ይገባል ነው ያሉት።
በመሆኑም ተቋማቱ በቅንጅት በመሥራት ለችግሮቹ መፍትሔ ማበጀት አለባቸው ነው ያሉት፡፡
ኢንቨስትመንት ሁሉንም የኢኮኖሚ መስኮች የሚዳስስ በመሆኑ ብሔራዊ ባንክ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመሆን ችግሮችን ለማቃለል እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
ከክልል ተሳታፊዎች መካከል የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዑመድ ኡጅሉ፤ በክልሉ ከመሬት አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚነሱ አከራካሪ የመመሪያና ሌሎች ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ያጋጠሙና የሚነሱ ችግሮችን በመቅረፍ የተሻለ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲኖር እንሰራለን ብለዋል።
ነገር ግን መሬትና ብድር ወስደው ውጤታማ ያልሆኑ ባለሃብቶች በመኖራቸው ምክንያት ከፈቃድ አሰጣጥ ጀምሮ ክትትል ማድረግ እንደሚገባም ነው ያነሱት፡፡
ከተመሰረተ አሥር ዓመታት ያስቆጠረ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የቅንጅት መድረክ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ የተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ የፋይናንስ ተቋማትና ጉምሩክን ጨምሮ በርካታ የፌዴራል ተቋማትን በአባልነት ያቀፈ አደረጃጀት ነው።
በቀጣይም ቅንጅታዊ አሰራሩን ለማጠናከርና የሚያጋጥሙ ችግሮችን በወቅቱ ለመቅረፍ የክልል እና ተጨማሪ የፌዴራል ተቋማት ተካተው እንደሚሰራ ተወስኗል።