ቀጥታ፡

አገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን የኃይማኖት አባቶች የአገር የሽማግሌዎችና የሰላም እናቶች የበኩላቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

መጋቢት 16/2014 (ኢዜአ) አገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን የኃይማኖት አባቶች የአገር የሽማግሌዎችና የሰላም እናቶች የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ጥሪ አቀረቡ።

አገራዊ  ምክክር ኮሚሽን ከኃይማኖት አባቶች፣ ከአገር የሽማግሌዎችና ከሰላም እናቶች ጋር የትውውቅና የጸሎት መርኃ ግብር አካሂዷል።

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽነሩ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ አገራዊ ምክክሩ የታለመለትን ግብ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት።

በተለይም ይህ ወሳኝ አገራዊ አጀንዳ እንዲሳካ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተሰሚነት ያላቸው የኃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ብዙ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የኃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ሕዝብ በማስተባበር ከሚያድረጉት አስተዋጽዖ ጎን ለጎን ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን በጸሎትም ማገዝ እንዳለባቸው ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ ባለብዙ ኃይማኖቶችና ሥርዓት ባለቤት እንደመሆኗ ለአገር ሰላምና ለዜጎች አንድነት የኃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ምክርና ጸሎት የግድ ያስፈልጋል ብለዋል።  

ቀደም ባሉት ግዜያት በአገሪቱ እየተከሰቱ ያሉ ችግሮ ወደ ተባባሰ ደረጃ ሳይደርሱ በአጭሩ ለመቋጨት የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሰላም እናቶች ሲተጉ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይህንን መልካም ተሞክሮ በዚሁ አገራዊ ምክክሩ ላይም አስተዋጿቸውን እንዲያበረክቱ ጠይቀው  የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ለምክክሩ ስኬታማነት የሚጠበቅባቸውን እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርበዋል።

በመርኃ ግብሩ 11ዱን ኮምሽነሮች ጨምሮ የሁሉም የኃይማኖት ተቋማት መሪዎችና የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባላት፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሰላም እናቶች ታድመዋል።

በመርኃ ግብሩ የታደሙ የሁሉም ኃይማኖት መሪዎች ለኮምሽኑ ሥራ ስኬታማነት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንደሚወጡ ጠቁመው ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን በጸሎትም ፈጣሪን እንደሚማጸኑ ገልጸዋል።

የተለያዩ ብሔረሰብ ተወካይ የሆኑ የአገር ሽማግሌዎችና የሰላም እናቶችም ኮምሽኑን በሚጠበቅባቸው ኃላፊነት በማገዝ ረገድ በጋራ ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

አገራዊ ምክክሩን በቀጣይ በቅርበት ለሚያግዙ አካላት የቀጣይ የሥራ መርኃ ግብር የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚከናወን በመድረኩ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም