" ከዒድ እስከ ዒድ ወደ አገር ቤት"መርሃ ግብር ላይ ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግቦችን ለማሳካት ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
" ከዒድ እስከ ዒድ ወደ አገር ቤት"መርሃ ግብር ላይ ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግቦችን ለማሳካት ይሰራል
መጋቢት 16 ቀን 2014 (ኢዜአ)ከዒድ እስከ ዒድ ወደ አገር ቤት "መርሃ ግብር ላይ ኢትዮጵያውያን፣ትውልደ ኢትዮጵያዊን፣የጎረቤት አገራት እና የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ዜጎችን በስፋት በማሳተፍ ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግቦችን ለማሳካት እንደሚሰራ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ ገለጹ።
" ከዒድ እስከ ዒድ " ጥሪን ለማስተባበር የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ ከጥሪው ጋር ተያይዞ የሚከናወኑ ተግባራትን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫው መርሃ ግብሩን ለማስተባበር በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ እና በኡስታዝ አቡበከር አህመድ በጥምረት የሚመራ እንዲሁም የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ፣የተለያዩ የፌደራል መስሪያ ቤቶች ሀላል ፕሮሞሽን እና ነጃሺ በጎ አድራጎት ማህበር ድርጅት በጣምራ ሴክሬታሪያትነት የሚቀናጁ አብይ እና ንዑስ ኮሚቴ መዋቀራቸው በመግለጫው ወቅት ተመልክቷል።
እንደ አምባሳደር ብርቱካን ገለጻም " ከዒድ እስከ ዒድ ወደ አገር ቤት " በሚለው መርሃ ግብር የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት ታላቅ የጎዳና ላይ ኢፍጣር ፣ታላቁ የኢድ ሰላት በኢትዮጵያ ፣ የተጎዱ ወገኖች ጉብኝትና ድጋፍ፣ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላና የበዓል ስጦታን ያካትታል ብለዋል።
በተጨማሪም ሲምፖዚየም እና ፎረሞች፣ ባዛርና የንግድ ትርዒቶች እንዲሁም የተለያዩ ሃይማኖታዊ ፣ባህላዊ እና የታላላቅ ፕሮጀክት ጉብኝትም ከመርሃ ግብሮቹ መካከል ስለመሆናቸውም ገልጸዋል።
በዚህ መርሃ ግብርም ኢትዮጵያውያን ፣ትውልደ ኢትዮጵያዊን ፣ የጎረቤት አገራት እና የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ዜጎችን በስፋት በማሳተፍ ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግቦችን ለማሳካት ይሰራል ብለዋል።
ኡስታዝ አቡበከር በበኩላቸው በመርሃ ግብሩ የእርስ በእርስ ግንኙነቶች የሚጠናከርበት ይሆናል ብለዋል።
ታላቁ " የኢድ ስግደት በኢትዮጵያ " ጥሪ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በቅርቡ ማስተላለፋቸው ይታወሳል።