በተለያዩ ቋንቋዎች የሚሰጠን ትምህርት ሥራ የማግኘት ዕድል ያሰፋልናል - ኢዜአ አማርኛ
በተለያዩ ቋንቋዎች የሚሰጠን ትምህርት ሥራ የማግኘት ዕድል ያሰፋልናል
ነገሌ፤ መጋቢት 16/2014(ኢዜአ) የነገሌ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በሀገር ውስጥና የውጭ ቋንቋዎች እየሰጠ የሚገኘው ትምህርት የተሻለ እውቀትና ሥራ የማግኘት ዕድል ያስገኝልናል ሲሉ የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ተናገሩ።
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በጉጂ ዞን ነገሌ ከተማ በ179 ሚሊዮን ብር ያስገነባው ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በሁለት የሀገር ውስጥና በአራት ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ትምህርት መስጠት ጀምሯል፡፡
ትምህርት ቤቱ ሥራ የጀመረው ከኦሮሚያ ክልል በስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገቡ ተማሪዎች አወዳድሮ በመቀበል እንደሆነ ተመልክቷል።
በትምህርት ቤቱ የመማር እድል ያገኘውና ከአሰላ ከተማ የመጣው ተማሪ ፉአድ አማና ከክልሉ ተማሪዎች ጋር ተወዳድሮ ትምህርት ቤቱን በመቀላቀል በፈረንሳይኛ ቋንቋ መሰረታዊ ዕውቀትና መደበኛ ትምህርቱን በመከታተል ላይ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡
ከአርሲ ዞን ዲክሲስ ወረዳ የመጣው ተማሪ ኤርሚያስ ፍቃዱ በበኩሉ "መሰረታዊና ጥልቀት ያለው ትምህርት ተገቢውን ዕውቀት ያስጨብጣል ተምሮም ስራ የመያዝ ዕድልን ያሰፋል" ብሏል፡፡
ተማሪ ሁንዳኦል አመንቴ በትምህርት ቤቱ የሚሰጡት ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች የተሻለ ዕውቀት ለመጨበጥ መነሳሳት እንደሚፈጥር ገልጿል።
ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቱ በተለያዩ ቋንቋዎች እየሰጣቸው ያለው ትምህርት የተሻለ እውቀትና የተለያዩ አማራጭ ያላቸው ሥራዎች የማግኘት ዕድል እንደሚያሳፋላቸው ነው ተማሪዎቹ በሰጡት አስተያየት የተናገሩት።
የጉጂ ዞን ትምህርት ጽህፈት ቤት የእቅድና በጀት ሃላፊ አቶ አንድነት አበበ ትምህርት ቤቱ ደረጃውን በ18 የመማሪያ ክፍሎች፣ በ1 ሺህ 200 የተማሪዎች ማደሪያ፣ ቤተ መጻህፍት፣ የስፖርት ማዘውተሪያ፣ የመሰብሰቢያና የመመገቢያ አዳራሾችን በማሟላት አገልግሎት እየሰጠ ነው ብለዋል።
ትምህርት ቤቱ ከክልሉ ሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች በስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ብቻ እንደሚማሩበት አስረድተውም ለመጀመሪያ ጊዜ ህዳር 13 ቀን 2014 ዓ.ም የላቀ ውጤት ያመጡ 159 ተማሪዎችን በመቀበል አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡
ከሀገር ውስጥ በአፋን ኦሮሞና አማርኛ፤ ከውጭ ደግሞ በእንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ዓረብኛና ቻይንኛ ቋንቋዎች ትምህርት እየተሰጠ መሆኑንም ገልጸዋል።
ትምህርት ቤቱ የተቀበላቸውን ተማሪዎች በ12 የትምህርት ዓይነቶች በሀገር ውስጥና በውጭ ቋንቋዎች እያስተማረ ነው ያሉት ደግሞ የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር አቶ ደረጃ ቶሎሳ ናቸው።
የተማሪዎቹ ሙሉ ወጪ በመንግሥት እንደሚሸፈን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ትምህርት ቤቱ በሂደት በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡ እስከ 1 ሺህ 200 ተማሪዎችን አወዳድሮ የመቀበል አቅም እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡