ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ በተለያዩ የልማት ዘርፎች ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረም ይካሄዳል

መጋቢት 16/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመት በቤት ልማት፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በአይ ሲቲና በግብርና ልማት እንዲሁም በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረም ይካሄዳል።

በፌዴራል የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን የሚዘጋጀው ይኸው ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረም ከሕዳር 24 እስከ 29/2015 ዓ.ም ለአምስት ቀናት በአዲስ አበባ ይካሄዳል ተብሏል።

በፎረሙ ከ250 በላይ በዘርፉ የተሰማሩ ዓለም አቀፍ ኩባንያ ተወካዮች እንዲሁም የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችንና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚታደሙ ይጠበቃል።

ፎረሙን በአካል ተገኝተው መከታተል የማይችሉ 500 ግለሰቦች ደግሞ በቬርቱዋል ወይንም በኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ታግዘው ካሉበት ሥፍራ የፎረሙ ታዳሚ እንደሚሆኑም ነው የጠቆመው።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ሌንሳ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የፎረሙ ዋና ዓላማ የውጭ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጮች ለማስተዋወቅ ነው።

ይህንንም ለማሳለጥ በፎረሙ ላይ የተለያዩ አውደ ርዕይዎች፣ ባዘሮችና እንዲሁም የአገሪቱን አጠቃላይ ኢንቨስትመንት ግንዛቤ የሚሰጡ የተለያዩ መረጃዎች ይቀርባሉ ብለዋል።  

ፎረሙ በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ የሚያስችል የተለያዩ ዝግጅቶች ከወዲሁ መጀመሩንም ጠቁመዋል።

በፎረሙም ላይ ባለኃብቶች በሽርክና ከኮርፖሬሽኑ ጋር በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በተለያዩ ልማት ሥራዎች እንዲሳተፉ ያግዛል ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በፎረሙ የሚሳተፉ ኢንቨስትሮች በአገሪቱ በሚገኙ የተለያዩ የቱሪስት መስህቦች እንዲጎበኙ ይደረጋል ሲሉም ጠቁመዋል።

የፎረሙ ተሳታፊዎች ከመጪው ሚያዚያ 23/2014 ዓ.ም እስከ መስከረም 1/2015 ዓ.ም በኦን ላይን ምዝገባ ማድረግ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

በፎረሙ የኢትዮጵያ መንግሥት ከተለያዩ የውጭ ኩባንያዎች ጋር ሁለት ቢሊዮን ዶላር ግምት ያለው ሦስት የኢንቨስትመንት ሥምምነትና አምስት የመግባቢያ ሥምምነት ይፈጽማል ተብሎ ይጠበቃል።    

የፌዴራል የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን በከተሞች የቤቶች ልማት፣ የአገልግሎት አሰጣጥና ከመሰረተ-ልማት ጋር የተያያዙ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም