ቀጥታ፡

ቤተክርስቲያኗ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ክልሎች መልሶ ለማቋቋም የሚውል ኘሮጀክት ይፋ አደረገች

መጋቢት 16/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ክልሎች መልሶ ለማቋቋም የሚውል ኘሮጀክት ይፋ አደረገች።

ፕሮጀክቱ በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋርና በኦሮሚያ ክልል በጦርነትና ጸጥታ መደፍረስ ምክንያት ለችግር የታዳረጉ የኀብረተሰብ ክፍሎችን መልሶ ለማቋቋም የሚውል ከ134 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዞለታል፡፡

በዚህም አጠቃላይ 227 ሺህ 255 ዜጎች ተጠቃሚ ያደርጋል ከዚህ ውስጥ 9 ሺህ 690 ህፃናት  መሆናቸው ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጸሀፊ ዶክተር አባ ተሾመ ፍቅሬ እንዳሉት፤ ቤተክርስቲያኗ በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች እርዳታ እያከናወነች ትገኛለች። 

ድጋፉ በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን የኀብረተሰብ ክፍሎች ችግር በማቃለል ወደ መደበኛ ህይወታቸው እንዲመለሱ ያግዛል ብለዋል፡፡

ቤተክርስቲያኗ ባለፈው ዓመት ሰባት ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የጤና፣ የትምህርት፣ የምግብ ዋስትና  የንጹህ መጠጥ ውሃ እና ሌሎች ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ማድረጓንም አስታውቃለች፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም