የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በትምህርት ቤቶች ለሚተገበረው የተማሪዎች ምገባ የ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በትምህርት ቤቶች ለሚተገበረው የተማሪዎች ምገባ የ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ ነሀሴ 29/2010 የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በአዲስ አበባ ከተማ አንደኛ ደረጃ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለሚተገበረው የተማሪዎች ምገባ መርሃ-ግብር ማስፈጸሚያ የ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ። የገንዘብ ድጋፉን የተመለከተው ስምምነት በድርጅቱ እና ''የእናት ወግ'' በተሰኘው አገር በቀል በጎ አድራጎት ማህበር መካከል ዛሬ ተፈርሟል። በዚሁ ወቅትም የማህበሩ መስራችና የበላይ ጠባቂ የቀድሞ የኢትዮጵያ ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ ተገኝተዋል። በመጪው ዓመት በማህበሩ አማካኝነት ተግባራዊ የሚሆነው የምገባ መርሃ-ግብር 500 የሚሆኑ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል። በዚህም መሰረት ተማሪዎቹ በየቀኑ ቁርስና ምሳ ይቀርብላቸዋል። ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ከሚገኙ 210 የአንደኛ ደረጃ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ለተውጣጡ 21 ሺህ ተማሪዎች የምገባ መርሃ-ግብር እየተተገበረ መሆኑን የማህበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ደብረወርቅ ልኡልሰገድ ተናግረዋል። ሌሎች አካላትም እነዚህ ድጋፍ የሚሹ ተማሪዎች የምግብ ዋስትናቸው ተረጋግጦ ትምህርታቸውን በተረጋጋና ዘላቂነት ባለው መንፈስ እንዲከታተሉ ለማድረግ የኢትዮጵያ መድን ድርጅትን ዓረአያነት በመከተል ሌሎች ግለሰቦችና ተቋማት ማህበሩን እንዲረዱ ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ነጻነት ለሜሳ በበኩላቸው፤ ድርጅታቸው የተጣለበትን ማህበራዊ ኃላፊነት ለመወጣት በማሰብ ከ''የእናት ወግ '' ማህበር ጋር በትብብር መሥራት የጀመረው በ2009 ዓ.ም መሆኑን አስታውሰዋል። ወደፊትም ለማህበሩ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። የማህበሩ መስራችና የበላይ ጠባቂ የቀድሞ የኢትዮጵያ ቀዳማዊ እመቤት ሮማን ተስፋዬ፤ አቅም የሌላቸውን ህጻናት ለማስተማር አጋር ድርጅቶች የጀመሩትን ድጋፍ እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።