ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በዓለም ተሰሚ እንድትሆንና ብሔራዊ ጥቅሟ ለማስከበር በትኩረት እንሰራለን

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በዓለም የበለጠ ተሰሚ እንድትሆንና ብሔራዊ ጥቅሟ ለማስከበር በትኩረት እንደሚሰሩ ኢትዮጵያን ወክለው በተለያዩ አገራት የተሾሙ አዳዲስ አምባሳደሮች ተናገሩ።

ኢትዮጵያን ወክለው በአሜሪካ፣ በኤርትራ፣ በኬንያና በኳታር የተሾሙ አምባሳደሮች በቀጣይ ስለሚኖራቸው የዲፕሎማሲ ተልዕኮ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ እንደገለጹት፤ ሁለቱ አገራት ከምዕተ-ዓመት የተሻገረ ጠንካራ ግንኙነት አላቸው።

በአምባሳደርነት ጊዜያቸውም ኢትዮጵያና አሜሪካ ያላቸውን ፍላጎት በማቀራረብ ሁለቱ አገራት ይበልጥ ግንኙነታቸው እንዲጠናከር በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በተለይም የኢትዮጵያን ጥቅም በሚያስከብርና ሁለቱም አገራት የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ ዲፕሎማሲያዊ ተግባር ለማከናወን መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በአሜሪካ የሕግ አውጭ ምክር ቤቶችና የአስተዳደር አካላት ተሰሚ እንድትሆን በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ማዕከል ያደረገ የፐብሊክና የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ይሰራል ብለዋል።

በተጓዳኝም በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ተመልሰው በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ መስኮች እንዲሳተፉም ትኩረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።

በኤርትራ የተሾሙት አዲሱ አምባሳደር ፍቃዱ በየነም ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ወደ መልካም ግንኙነት የተመለሰውን የአገራቱን ወዳጅነት በተለያዩ መስኮች ለማጠናከር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ሁለቱ አገራት በተለይም በሰላም፣ በንግድና በኢኮኖሚ ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖራቸው ትኩረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አምባሳደር ባጫ ደበሌም፤ "በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባውን በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማስቀጠል እሰራለሁ" ብለዋል።

በአገራቱ መካከል የተፈረሙ የሁለትዮሽ ሥምምነቶችን ወደ ተግባር በመቀየርም አዳዲስ ጥቅሞችና ቀጣናዊ ትብብሮች እንዲፈጠሩ ለማድረግ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

በኳታር የኢትዮጵያ አምባሳደር ፈይሰል አሊይ በበኩላቸው "በሁለቱ አገራት መካከል የተፈረሙና በሂደት ላይ ያሉ ከ13 በላይ ሥምምነቶችን ወደ ተግባር እንዲለወጡ እተጋለው" ነው ያሉት።

አምባሳደር ባጫና አምባሳደር ፍቃዱ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ያላትን ትብብር እንድታጠናከር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በተለይም በሰላምና በኢኮኖሚያዊ መስኮች ቀጣናዊ ትብብሩ እንዲጠናከር ከአገራቱ መሪዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚንቀሳቀሱም እንዲሁ።

አዲስ ተሿሚ አምባሳደሮቹ አክለውም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን መብት ማስከበር ቀዳሚ ሥራቸው መሆኑን አንስተዋል።

ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን በማስተዋወቅ የውጭ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ገፅታ የመገንባትና የውጭ አገራት ጎብኝዎችን ወደ ኢትዮጵያ የመሳብ ሥራም ሌላኛው ተልዕኳቸው መሆኑን ነው ያረጋገጡት።

ኢትዮጵያ ባሳለፍነው ሳምንት በውጭ አገር ሆነው የሚሰሩ 13 አምባሳደሮችን፣ በአገር ውስጥ የሚሰሩ አምስት አምባሳደሮች፣ አራት የቆንስላ ኃላፊዎችንና ዘጠኝ ምክትል ሚሲዮን መሪዎችን መመደቧ ይታወቃል።

አምባሳደሮቹ ትናንት በኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሹመት ደብዳቤና የሥራ መመሪያ የተሰጣቸው ሲሆን ኢትዮጵያን በታማኝነት ለማገልገልም ቃለ መኃላ ፈፅመዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣

እንዘጋጅሀገርን በዘላቂነት እናልማ

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም